Categories
መልካም ጥበብዎች Fine Arts

አዙሪት ዘአልፋ፤ የለውጥ ጸር ለውጥን ሲመኝ

Belay Manaye’s Azurit ZeAlpha, a Novel, fan reviewed.


A potential murdered; so oxymoron it is. It is plotless plot. And, a no-story story. Quite self-contradictory and a theme that is too-archaic-and-full-of-fool-judgments. At its best no-that-much and nearly nothing-at-all tale. Itself as embarrassing illusion as the null illusion in it. Simply, and in conclusion, a-not-helping-at-all too outdated telling.


bY Binyam Hailemeskel Kidane, 2013 ዓም፨

የተዋዳጅ ሂስ፤ (Fan Review)


ይህም አጭር ያልተሟላ ዳሠሳ ሲሆን፤ በጣም አጠር ባለ መንገድ የተበጀውን የተዋዳጅ (አንባቢ) ሂስ በሌላ ጊዜ እንመለስበት አለን። [አሁን ያንን ሁለተኛ እትም እዚህ የአግኙ]


ደራሲ፦ በላይ ማናዬ (ጋዜጠኛ፣ ፓለቲከኛ)፤ ርእስ፦ አዙሪት ዘአልፋ፤ ህትመት፦ 2005 ዓም፤ አታሚ፦ አልተገለፀም፤ አሳታሚ፦ አልተገለፀም፤ ዋጋ፦ 55 ኢብ.፨

[“ትልቁ ችግርአችን ምን መሰለህ…የዱላ ቅብብሉ ድል የጋራ ዉጤት የጋራ ስራ መሆኑን ማመኑን አለማመን ይታይብን አለ። ወይም ደግሞ ዱላውን ተቀብለን ከመሮጥ ይልቅ ሳይቀበሉ መጣል። ከመስመር መውጣት። የቀደመው ሯጭ የሰራውን ስራ መናድ ይታይብን አለ። ከነበረው ሰዓት ላይ የተሻለ አስመዝግቦ ማሸነፍ ሲቻል ሙሉ ለሙሉ እንደ አዲስ መጀመር።….” (ገ.119)]


ሴራ ጭምቅ


በአዲስአበባ ኅዋአዊከተማ (university)፣ ዋናው ጊቢ ስድስትኪሎላይ፣ አብርሀም ምናለ ህግ ተማሪ ነው። ከጎጃም ጭምባ መንደር የመጣው፣ በሴት ቢፈቀርም ፆታ-ፍቅር-እማይገባው፣ እጅግ ትምህርት ላይብቻ አተኳሪ ነው። የተፈጥሮ ጉጉቱ እና ስሜቱ፣ ወደ ማህበረሰብ አስተዳደር ጉዳይዎች እና እንቅስቃሴዎች ይወስደዋል። (ግን ያ አዝማሚያ ያለው ተማሪ ሁሉ እሚያረገው ባይሆንም) አዙሪት እሚሰኝ የሠላሣ ዓመት እድሜ ያለው በጊቢው የህግ መምህር እና ዳያስፖራ ዶክተር አልፋ አስጨናቂ መሪነት ከብዙ የውጭ ምሁራን ድጋፍ ጋር እሚሰራ የረቀቀ ህቡዕማህበር (secret society) አባል ነው። ተቋሙ አንዴ ለጥቂት እሚያስመለክተንን የባህርዳር ድብቅ ልዩ-ዝሙን መስሪያቤቱን ጨምሮ በእየክፍለሀገሩ ከርሰምድር እና ዋሻዎች ዉስጥ የተቀበሩ ብዙ የረቀቁ ሽልፍኖትዎች (technologies) እንደእሚገለገል ይናገራል። እና ተሰውሮ የሀገርአችንን ደህንነት እና ዕድገት እሚጠባበቅ በስውር-መልካም አድራጊ ድርጅት ነው።
አብርሀም አዳዲስ አባልዎች ለስውር ድርጅቱ ሲመለምል፣ የፖለቲካል ሳይንስ ተማሪውን ቀልቤሳ ወይም ደስ በእሚል ቅጽሉ “ኢትዮጵያአዊው ማርክስ” እሚሰኝ የመንገድ-ዳር-አርበኛን ይመለምላል። እሱም፤ በእብድ ደንብ ለተለያዩ አገልግሎቶች ተሰልፈው እና ተሰብሥበው የሚቆሙ ወጭወራጅ ዜጎችን ሁሉ በመንገድ-ዳር ስብከቱ ስለ ሀገርአዊ የፖለቲካ ተሳትፎ እና ማህበረሰብአዊ ንቁ-እንቅሥቃሴ በመስበክ ንቃተህሊናአቸውን በማንቃት ይታወቃል። ከስሙ ግምባር ስጋ እንደሆነው፤ ንቁ ማህበረሰብአዊ የዜጋአዊያ (civilian) ተሳትፎ እና ሀገርአዊ ስልጣኔን ማመንጨት በአንክሮትአዊ (critical) ስብከትዎቹ ወደ ንቃት ይሰብካል።
ሀበን ከአድዋ ከተማ የመጣችው ተማሪ ደግሞ በመማር ማስተማር ክበብ የተቀራረበችው እና እምታፈቅረው እሱ ግን እማያፈቅራት፤ የክበቡ መሪ ስለሆነ ከስሩ የምትሰራ ስለሆነ የሚገናኛት ተማሪ ናት። ሁለተኛደረጃ ባህርዳር ሲማር፣ ኃይማኖት’ የምትሰኝ ልጅ አፍቅሮ ልቡ ስለ ተሰበረ ሌላ አያስብም። ያንን ቢያሳውቃት እና ባይሳካላትም ለፍቅር ከመዘብዘብ ግን ቸላ አትልም።
በመጨረሻ ትርክቱ ሲቋጭ፣ ታግላ ታግላ ማሯን አገኘች። ኃይማኖትን ረስቶ ለእሷ ግድሰጥቶ ድንግልናአቸውን በመረካከብ የመቀራረብ ሁኔታቸው ተፈፀመ።
በሌላው የሴራው ክንፍ፣ ዶክተር አልፋ በዘመንአዊ ምናብቴአዊ (of fantacy) ስውር መሰብሰቢያ ቦታዎችአቸው ተጨማሪ ወጣትዎችን ለመላ ሀገሪቷ ቅርንጫፎችአቸው መለመሉ። ለቀረበው የ2005 ብሔርአዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምርጫ፣ የህዝብ ድምፅን፣ እና ሰላምን፣ ለማስከበር እና አዙሪትን እንዲወርሱ እንዲዘጋጁ ተመልማዮቹን አባሎች አሳወቀ።
የትልሙ ፀረአቀንቃኝ እጅግ ዘግይቶ ከተፍ ይላል። እርገጤ፣ አነፍናፊ የሆነ አመንግስት ደህንነት እና ለአለቃዎቹ ጉብዝናውን አሳይቶ እውቅና መቀበል እሚሻ ሠላይ ሰራተኛ ነው። ደግ-አሳዳጅ (vigilante) ስራአቸውን እሚያስጠረጥር ኩነቶች ተደራረቡበት እና ያነፈንፋቸው ጀመረ።
አዙሪቶች እንደሆኑ ባያቅም፣ አንድ የግብፅ ሰላይን እንደመጣ ባህርዳር የሆኑ ሀገር ወዳዶች ለቅመውት፣ ዝተው፣ ፎክረው እና አስፈራርተው ወደሀገሩ እንዲመለስ ማድረጋቸውን ሠማ። ወዲያው አሁንም አንድ ቡድን የእርዳታ ስንዴ የሰረቁ ባለስልጣንዎችን በሌሊት ሲጓዙ አስቁመው አስረው ለህግዘብ (police) በመጋበዝ እና በመሰወር ሀገር በድብቅ አገዙ። እንዲሁም የሆኑ ግድያዎች ድንበር ላይ ስለተከሰቱ የደህነነቱ ሰራተኛ እርገጤ እጅግ የሀገር ጥበቃ ከዋኙን ድብቅ ቡድን ለማወቅ በመታተር ሲያጣው ይበሳጭ እና ለማግኘት ሊያነፈንፍ ይቆርጣል። ደህንነት ሰራተኛዎቹ በደግ-አሳዳጆቹ ስራ ግራ ተጋብተው ቡድኑን ለማወቅ ሲቋምጡ፤ እርገጤ ግን በብዛት ማሳደዱን ቀጠለ። ዳሩ፣ ያገኘው መረጃ አንድ ፍንጭ ብቻ ነው። አንድ የህቡዕማህበሩ አባል በስድስትኪሎ ዋናጊቢ ዶርም ተኝቶ በእንቅልፍ ልቡ ስለ አዙሪት ስለቃዠ እና በደህንነቱ ስር እሚሰሩ ተማሪዎች በድምፅ ቀርፀው የተናገረውን ጧት ሲነግሩት እራሱን ቀጭቶ በመሞቱ፣ የሆነ እውቅናየለሽ ድርጅት በእርግጥም እንዳለ ገመተ።
ከዶክተር አልፋ አለቅጥ እሚቀራረቡ ተማሪዎች ስላሉ፣ እየመረመረ፣ በማሳደዱ በመጨረሻ አስተማሪው ዶክተር አልፋ የ አዙሪት መስራቹ መሆናቸውን አወቀ። ሊይዛቸውም ፈለገ።
መምህሩ፤ አሳዳጅአቸው እርገጤን ማነፍነፉን አወቁ፤ ምስጋና ለመንግስት-ቅጥረኞችአቸው። ለሠላሣ አመት ቢደበቁም፣ ቤተሰቡም የተሰወረ ቢሆንም፣ ሊደረስባቸው እየተቀራረበ መጣ። በመጨረሻ፣ የዘመነውን ተቋም ከእሚመጣው አደጋ እንዳይጠብቅአቸው እና እርገጤንም በመጉዳት ወንድም ለወንድም (ዜጋ ለዜጋ) እንዳይጎዳዱ እና የሀበሻ ታሪክ እንዲቀየር ስለእሚፈልጉ፣ አዙሪትም አላማው ወንድማማችነት ስለነበር እርገጤን ከመመከት ለመያዝ እንደእሚመርጡ ነግረው፣ ተተኪዎችን አበጁ።
ምርጫውም እስኪቃረብ እርገጤ በጠሚ. ደህንነት አማካሪ ጭምር እና የደህንነት ቢሮ ኃላፊው ኃይላይ፤ አለቃው፤ ተደግፎ ዶክተሩን ሊያስር ዋናጊቢ ድረስ ተሰናድቶ ደረሰ። አንጡራ የልብወለዱ ቅንጭብ ጡዘቱ መጣ።
ዶክተሩ አባሎች እርገጤን እናጥቃ ቢሉም እጅ በመስጠት ሀሳብ ግትር ብለው የድርጅቱን አላማ ወንድምዎችን አለመጉዳት በእሚል ለመታሰር ይወጣሉ። ዳሩ የመንግስት ደህንነት ኃላፊው ኃይላይ በ አዙሪት አዲስ አባልነት ተመልምሎ ስድስትኪሎ ጊቢ ለማሰር የተሰናዳውን እርገጤን ልክ ሊያስር ሲል እራሱ እርገጤን ጥይት ሲደቅንበት፣ አልፋም ወደእንጦጦው ድብቁ ቤትአቸው እንዳላየ ነዱ።
ምርጫው ተከናውኖ ሰኞ በማግስቱ፣ ሰላም እንደሆነ ኢትዮጵያም አድናቆት እንደጎረፈላት ፍፁም ምናብቴው የበለጠውን ቅዠት ቃዥቶ ተቋጨ።


የተዋዳጅ ሂስ (Fan Review)


ባለ-ብዙ-ትላልቅ-ስህተትዎች የምናብቴ (fantasy) በር ላይ ቆሞ የተመለሠ ልብወለዱ፣ እጅግ ብዙ ክፍተቶች አሉት። ሲጀመር ይህን የደከመ ይዘት ላቅርብ ባይ ልብወለድ መኼሰሥ አይቻልም። እንደ መንገደኛ ተዋዳጅ (fan) እንኳ መተቸት ረብየለሽ በመሆኑ ከባድ ስራ ነው። ግን አንደኛ ከእማያረካ ስራ አተቻቸት ብዙ መማር ይቻል አለ። ሁለተኛ፤ በአስገራሚ ሁኔታ፤ ብዙ ይዘትአዊ ያልሆኑ ቢሆኑም (ጭራሽ እሚሻሉ ነገርዎች ያሉበት) ደህና ጎንዎች በእርግጥ አሉት። ሦስተኛ እምቅ አቅም በልብወለዱ ባይገኝም በደራሲው መኖሩ እሚታይ ነው። ስለእዚህ እንየው። ካየን፤ ከበጎ ነገርዎቹ መነሳቱ አስገዳጅ ነው።

ደግ ጎንዎቹ


አንደኛ፤ ልብወለዱ ሲያልቅ ከብስጭትአችን ጎን በጎውን ስናነስስ ከሁሉ ቀድመን ደራሲው የትርክት አወቃቀር ወይም አቀማመር (story structuring) አቅሙን በእምቅነት (potentially) ሊያሳየን መጣሩን እንረዳ አለን። የቀመራቸው ገፀባህሪዎች እንደ እጅግ መነሻነት እሚከፉ አይሆኑም። በትርክቱ ያላቸው ሚና ላይ ያደረገው ጠቅላላ ቀመሩ ደግ ነው። የሙሉ ትርክት ስሌቱ ደራሲው የስነጽሑፍ ክሂሎትአማአዊነት (technique) በእማያስከፋ መጠን እንደከወነ አስረጂ ነው። የመተረክ ፍላጎቱ እና ትትረቱ አብዝቶ አያስከፋንም።
በጠቅላላው፤ የትርክት ገፀእይታው (framework) አቀማመሩ እንደ መልካሙ አቅሙ እሚታይ ምንምአይሌ (fair) የሆነ ስኬቱ ነው። ለወደፊት ከተጠቀመው፤ የመፃፍ አቅም እንዳለው ግልጥ ነው።
ሁለተኛው፤ ቋንቋ አጠቃቀሙ እስኪያልቅ ቀላልነቱን አይተውም። የቀላል ቋንቋ አማርኛ አቀጣጠር ስልቱ (simple Amharic language style) ላልተሳካለት ሴራ እና ጥሬ-ጭብጡ ሙሉበሙሉ ጨካኝ ነገር እንዳይመሠክሩ፤ ለደራሲው መባባትን ያስገድዳል። አማርኛ ልብወለድዎችን በቅርብ ዘመንዎች እሚያነብብ ግለሰብ ባልሆንም አንዳንድዎችን ግን ሞካክሬ ነበር። ከገጠሙኝ ብዙዎች፤ እጅግ ቀላሉን አማርኛ ያየሁት ግን እዚህ ነው። ቀላል ቋንቋን ሁሉም መጠቀም የለበትም። የዘይቤ ወይም ስልት ዉሳኔ ነው። ግን፤ በፈለጉት የቋንቋ አቀጣጠር እሚጽፉልን፤ እንዳሻአቸው ቢጽፉም፤ የቋንቋን ዉብ ፍሰት ግን እምብዛም አያቀምሱንም።
ይኽኛው ልብወለድ፤ መነበብ ካለበት ለአንድ ኢላማ ቢሆን አንገት አያስደፋም። ያም፤ የቀላል አማርኛ አፈሣሰስን ስለምንመለከትበት ነው። በነጽጽር መሠል ብዙም ስለማያገኝ ያ ስኬቱ ብቸኛው ደግ ስኬቱ ነው። እሚነበበው ለውጥ እማያመጣ፣ እማይረዳ እና እማያግዝ እና ተርታ ይዘት ቢሆንም፤ ቀላል አማርኛን ለመመልከት በእሚል ማንበቡ ግን እሚከፋ አይደለም። ምንአልባት፤ የቋንቋን አቅልሎ እንደ ተርታ የጉንጭአልፋ አወራር መቅጠር እና በቋንቋው አሰልቺ አለመሆንን ለማስተማር ምርጡ መመራመሪያ መጽሐፍ ሊሆን እሚችል ነው። እምብዛም በማይጻፍበት ሀገርም ሆነ ቋንቋ፤ ይህን መጽሐፍ ለቀላል አማርኛ ዘይቤ መመራመሪያነት መጋበዝ አስፈላጊ ነው። መተኮር ያለበት መረሳት የሌለበት አስተያየትኤ (commentary) ቢሆን ደስ ይለኝ አለ።
ቀጥሎ አርትዖትአዊ ኢ-ኢትዮጵያአዊ ጭንቀቱን እናድንቅ። የአማርኛ ልብወለድዎች፣ በጠቅላላው ጽሑፍዎች፣ ለአርትዖተ-ፅሕፈት የለሽዴንታ በመሆን በተለይ በእዚህ መንግስት (ድህረ-ደርግ) እንዳበገኑን ናቸው። ዕድአዊ (manual) እትመት ዘዴ ከተለየን ወዲህ አሀዝአዊ ትየባ እና እትመት ዝማኔአችን በምጸትአዊ ውጤት እምናያቸውን የጽሑፍ ምርቶች እንደ ይዘትአቸው አቅለሽላሽ አድርጓል። ጀምረው እማይቋጩ አነ.ዎች፣ እማይከበሩ የህዳግ እና አንቀጽ ህገደምብዎች (protocols)፣ የቃልዎች ሰቅጣጭ ወጥነት እጦት ያሰቃየው ገጽ፤ በጠቅላላው ያልተማረ የአፃፃፍ ምርት እንደተጋትን ነን። ትልልቅ እሚሰኙ፤ ቢያንስ ከአለው ገበያ አንፃር፤ ልብወለድዎች እኒህን እልህ-ቀሚ ስህተትዎች በእየገፅአቸው በትነው እሚቀርቡን ናቸው።
በላይ ማናዬ ዉብ ጭንቀቱ በመጨረሻ ሙሉበሙሉ ባይሳካለትም፤ ጥንካሬን በጉዳዩ አስመልክቷል። በእየስፍራው ከተበተኑ የአንድ ፊደል በአንድ ቃል መሀከል ግድፈትዎች፣ የአዲስ መስመር አጀማመር ወጥነት ማጣት፣ እና አነስ ያሉ ሌላ ስህተርዎች በቀረ እማያስከፋ ገጽዎች ለማምረት ተጣጥሯል። ያ እንደተሰቃየለት ሰው፣ እጅግ አኩሪ ሊሆንለት እሚችል ነው። ለእኛም ደግ እምንለው ሙከራ ነው።
በእዚህ ጽሕፈት አርትዖት ዙሪያ ጭራሽ የተራመደው ነጥብም ግን አለ። አንድ ስላቅ ደራሲው በሁላችን ተሳልቋል። አልዘመነም እምንለው ጥንትአዊው አማርኛ፤ አለምክንያት አይደለም። ትክክለኛ የትእምርተ ስላቅ ምልክት በድንቁ እና በደፈናው በባይተዋሩ ቁምፊ (font) ኒያላ ውስጥ እንኳ የለንም። አይገርምም¡ አሁን ይህን ምልክት እንዴት እንደልብ እንጣው። ደስእሚለው ይህንን አንድ ሁለቴ ሦስቴ በላይ ተጠቅሞ (ም. ገ.124)፤ ለፌዝዎቹ ሁሉ “i” [አይ] እሚለውን አናባቢ እንግሊዝኛ ሆሄ ብዙጊዜ ይደረድርልናል። ይህ የልብወለዱ ምርጡ ምናብቴአዊ ይዉሰዱታ ነው። የመቀመሪያ-ማቀነባበሪያዎች (software) ባለሙያዎችአችን አማርኛን እንደመንግስት እና ህቡዕማህበሩ ቤተእንደራሴአችን ችላ ባለማለት የመክሊትአቸውን ቢያንስ ደግሞ የባንዲራፍቅር ወይም የዜግነትአቸውን ይወጡ። ቁምፊዎች ድንገት ብልጭ ብሎበት ለባነነ ደራሲ አላመች ብለው አይን ስንጠቀም የእልፍ ዘመንዎች ስልጣኔ ባለንብረትአማነትአችንን ዘወር ካላለብን ለመቀበል ያዳግተናል። ለእዚህ ጮማ ሙከራው፤ ከምኑምከምኑም ጫር ብቻ አለው። ስነእናኪነ (art) የገሀድ እና ጉራንጉር ችግርዎችን እየደፋፈንን እና እየሸፈንን እምንዘምንበት የመዝመረጃ (infotainment) መሳሪያችን ነው። ከሆነ፤ ይህ ቁምነገር ምርአዊ (series) ፊቱን አሳይቶን አንገት ደፍተን ወደመኝታ እምንገባ እንደሆነ፤ በልብወለዱ ባይሳካ በእዚህ እንደተፈነከትን እንመን።

ክፍተትዎቹ


እምቅ አቅሙ ግን በእዚህ ልብወለድ ከመገለጡ በቀረ፣ የተሳካለት ልብወለድ ግን ከቶ አይደለም። ከእዛ ጭራሽ የራቀ ነው፤ ኧረ-ወዲያ-ወዲያ አይነት ልብወለድ። ችግሩን ለመድፈን ብንሞክር ዝርዝርዎቹ እሚያስተምሩን ስለሆነም ጉድለቶቹን ቀጥለን ደግሞ እንጥቀስ።
ቀለል ካለው የሴራ አለመሳካት አንድ መገለጫ፤ የመጨረሻው ጡዘት ብንነሳ እንኳ፤ ተደራሲን በግልጥ የማታለል ሙከራውን እናገኛለን። ያም ከቶ የደራሲ ስነምግባርአዊ አካሄድ አይደለም። ጋጠወጥ ነው። ዶክተር አልፋ እንደእሚያዙ አውቀው ተማሪዎችን ለመጨረሻጊዜ አስተምረው ሲጨርሱ – በጡዘቱ መፍታቶት (climax’s resolution) ወቅት – እጅ ሊሰጡ ነው አለን። ዳሩ፤ ልክ ለመታሰር ሲወጡ እርገጤ አሳሪያቸውን በኩራት አዩት። አጠገቡ የነበረ አለቃው ኃይላይን ጠቀስ አደረጉ። እርገጤ ጥይት ተደግኖበት እሳቸው አርፈው ወደቤታቸው መኪናቸውን ነዱ።
ይህ ተደራሲውን ያታልላል። አለ አንድአች ትልም ማለትም አለአንድአች አመክንዮ የተፈጠረ ልብማንጠልጠል ነው። ተደራሲን ማታለል ደግሞ ብልህ አተራረክ አይደለም። ደራሲው ሁሉን አወቅ አንጻር ተራኪአችን ነው። እሚለንን ሁሉ እያመንን ነው ከሀ ጀምረን እምናነብበው። አሁንም ሲያልቅ፤ እጅ ሰጥተው ሊታሰሩ ወጡ አለን። በአመጣጡ እና አጨራረሱ ልብአችን ባይንጠለጠልም ይልቁንም ቢበሳጭም ብቻ ልብግን እሚያንጠለጥል እንደሆነ ታስቦልን ተነገረን። እንደተደራሲ ደራሲውን አመንን። አቀንቀኙ ሲወጣ ግን ትልሙ ሳይሆን እሚያስደምመን የደራሲው ሽምጥጥ ያለ ክህደት ነው። ወደሌላ መስመር አለምክንያት አቀንቃኝአችንን ሸኘው። ለምን – መመለስ ከቻለ – ሊያዙ ወጡ አለን (ከእዛ ግን አልተያዙም)? እጅግ የአፃፃፍ ስነምግባር እማይደግፈው መደበኛ ህግ ቢኖር እንደ ህዝብ ማታለል አስቀጪ መሆን እሚችል ትልም ጥምዘዛ ነው። ስንፍናውን እና ማጭበርበሩን እነሆ አለፍን።
ግን አንድ እማይመስልም ቢሆን አማራጭ አተረጓጎም ለማሳብ እንገደድ ይሆናል። እኛን ለማታለል ሳይሆን፣ ያስገቡት መልእክት “አልታሰርም! ላሳስረው ነው! ብጎዳ ድንገት ቻው!” ከሆነ፤ ትርክቱን እጅግ ሳቢ ያልሆነ ያደርገዋል። ምንም ዉጣውረድን እማናይበት እና ድልአድራጊነት እንደዘበት እሚታፈስበት ያልጎመራ አተራረክ ያደርገዋል። የሙሉ ልብወለዱ ጡዘቱ “ከተጎዳሁ ቻው፤ አልተጎዳሁም ትርክቱ አለቀ” ከሆነ፤ ያልተጀመረ ልብወለድ ሆኖ ያልቃል። ያለ ከፍተኛ ግጭት፣ ጡዘት እና ብልህ አፈታቱ፤ ምኑም ሴራ መማረክ አይችልም። አጨራረሡ፤ ወይም አታላይ ወይም ደካማ ነው!

ያ ግን፤ የመግቢያ ስህተት ነው። ትልቅ ከእዛ እሚያያዝ የትልም ግጭት እና ችግር አለ። እስከመጨረሻ፤ እሚሰበከው እና ከምንም በላይ ትርክቱ እሚጎለብተው እና እስከፍፃሜ እሚጓዘው የዶክተሩ ማንንም ሰው ከቶ አለመንካት ፍልስፍና ነው። የ አዙሪት ትልቅ መርኅም ጭምር ነው። ደጋግሞ እና ተደጋግሞ የእሚነገረን እና እምንሰለቸው ድግግሞሽ ድረስ የተረጋገጠልን ነበር። ነገርግን፤ በመጨረሻ፤ አለምንም አመክንዮ፤ ደጋግመው አንነካውም ያሉትን እርገጤ፣ “ስራውን ስለሰራ ብቻ” ወደ ሽጉጥ መደገን እና መከዳት ፍፃሜ ያደርሱታል። የልብወለዱን ለትልሙ ያለውን ሀቀኛነት ግራአጋቢ ያደርጋል። እራሱን ከእራሱ ያጣርሰዋል። የሰበከውን የተቋሙ መርኅ የአንድም ሀበሻ ሌላ ሀበሻን አይነካም ዋና ትርክት ወንጌል እራሱ ያከሽፈዋል። ያ፤ ብልህ ሴራ አተራረክ አይመስልም። ከህዝብ የተደበቀ አሠራርን ለተጠያቂ አሠራር ለማብቃቱ እና ሀገር ማገዙ እና ሀላፊነቱን የተወጣ ዜጋነቱ፤ ተሸናፊ ተደርገለ መመልከቱ ምኑም ለጭንቅላት የተሸከመ አንባቢ አርኪ መሆን አይችልም። ፀረአቀንቃኝ ሳይሆን መደበኛ ግለሰብ ሲሸነፍ ማንበብ ቢያንስቢያንስ ሰቅጣጭ ባይሆን ያን ያክል አርኪ አይሆንም። ደራሲው የስነምግባር ኮምፓስአችን እየጠበቀን ያዘበራርቀው አለ።
ሦስተኛ፤ ወደዋናው አብሮ ያለ ሌላ ትልቅ የሴራ ክፍተት እንምጣ። ያም ዶክተር አልፋ፤ መኖሪያቤትአቸው እንኳ አለመታወቁ እና ምንም ምስጢርአቸው ተገልጦ በተግባር ላይ ለገሀዱ አለመገኘቱ ነው። የእርገጤ እነ ዶክተር አልፋን ማነፍነፍ ሂደት የደረሰበት ነገር ቢኖር ዶክተሩ ልዩ ተቋም ነገር እንዳላቸው ማውጠንጠኑ (contemplation) ነው። ምንም ሌላ ነገር እንዳልተደረሰብአቸው ይታወቃል። እጅግ የተደበቁ እና ጥብቅ ተቋም ናቸው። ስለእዚህ፤ አለትልም ብዙ ነገር ተነገረን እንጂ ደራሲው መፈናፈኛ የሌለው ነው።
ለምሳሌ፤ ዶክተሩ ምንም እማይታወቅብአቸው ከሆነ ታዲያ ለምን እጅ አይሰጡም? ምን ስጋት አለባቸው? አንድም ተጨባጭ መረጃ እርገጤ የለውም! እንኳን ድርጅቶቹ መኖሪያቤታቸውን ማወቅ አልቻለም። በተራ ነውታ (claim) የተደበቀ ትልቅ ምስጢርአዊ ድርጅት አላቸው ቢል፤ አለቃው እንዳላመኑት ቀደምሲል እንደተነገረን፤ ሌላም ኃላፊ ስለማይሰማው፤ ወዲያው በነፃ ይለቀቁ ነበር። ማስረጃ በሌለበት ምንም ጥርጣሬ መግፋት ስለማይችል። ቢመረመሩም በመካድ “ከማስተማር በቀረ ኧረ የምን ምስጢር ድርጅት ነው!” ብለው አሳሥቀው ሁሉ ይለቀቃሉ። ካላመኑ፤ ምንም የያዘው ማስረጃ የለም። ለምን ተጨነቁ? በትርክቱ ጉዞ ለምን እሚለው እንቅስቃሴው ካልመለሠው፤ ኦና ሴራ ነው። አለሴራ ያለ ልብወለድ ማንበብ ምንም ልብወለድ ከማንበብ ፈጽሞ እኩል ነው። ገሀድን አያንጸባርቅም። ከሆነ፤ ትርክቱ ቅዠት እና ስካር ነው። ልክ እንደሆነው።
ያንን ሳንጠቀልል አማራጭአችንን እንድገም። ልብወለዱ አበክሮ እሚደጋግምልን ወሬ አለ። ድርጅቱ፤ ከፍተኛ የመንግስት አገልጋዮችን ጭምር የያዘ ነው። ከሆነ፤ ለምን ዶግማ-መርኁን ከመጣሥ፣ ማስረጃ ከቶ ስለሌለው እንዲያቆም አያደርጉትም? ድርጅቱ፤ በማይጠረጠሩ ቦታዎች በስውር እሚሰራ ስለሆነ ምንም እንዳልተገኘበት፣ በመጨረሻም ምንም አይገኝበትም። ያን እንዲያግዙ ባባለስልጣናቱ እሚጠየቁ ከሆነ፤ የተሰበከለት የልብወለዱ ጭብጥ ተዙሮ አይጠረስም ነበር። ያንን አማራጭ ባለመከተሉ አጉል አንዱን ለመጉዳት በመሯሯጡ እጅግ የግጥምአዊነት ፍትህ (Poetic Justice) የፈረሰበት አይነተኛ ትርክት ነው።
ሌላው፤ ወጥ የሆነ አተራረክ እና ዘውግ ማጣቱ ነው። ምናብቴ እንዳይሉት ገና የዘውግ በሩን ረግጦ የተመለሰ እንጂ ወደዘውጉ ድንበር የተሻገረ አይደለም። የሰላይዎች ልብአንጠልጣይ (spy triller) እንዳንለው አልፎአልፎ ካለአመክንዮ ያንን መከወኑ እንጂ ወጥ አድርጎ የያዘው ወይም ሴራ ያበጀለት ስለላ አይታይም እና ከቶ ያ ዘውግም አይደለም። ደግ-አሳዳጅ ድረረጊትአዊ (vigilante action) እንዳንለው አንዴ ሲጀመር ያንን አስጮለቀ እንጂ ግብጽአዊው ከተሸኘ በኋላ ደግሞ ዞር አይልበትም። የፍቅር ትርክት እንዳንለው እጅግ በእየስፍራው ከላይ ከተጠቀሱት ዘውግዎች እየተቀያየረ እንጂ አንዴ ሲፈሥስ አናየውም። በተለየ መልኩ የስነውሳኔ (politics) እና ምርጫ ጭብጥ እሚሸከምም አይደለም። ያ ሲያበቃ አካባቢ የተከወነ ነው። ይህም አንድ መስተካከል ያለበት ጉዳይ ነው።
በጠቅላላው፤ ይህ እሚያሳየን ትርክቱ አንድ መስመር አይዝም፤ እምለው ከገባችሁ። እንደእምቦሳ’ እዚህእዚያ እያለ፣ ለመተረክ ይቅበዘበዛል። እኛ መዘበራረቁን ብንቀናንስ እና ብናጠልለው እሚደፋው ግን፤ ሴራየለሹ የሰላይ አለመረጃ ተሠላይን አደና ትርክት ነው።
ሌላው ለአንባቢያን የእድሜገደብ አለማበጀቱ እንደ ስህተት ነው። ሲጀመር ገና ምንም በቂ ሴራ አናገኝበትም። ለጎልማሣ እሚሆን ልብወለድነት የለውም ማለት ነው። ለልጅ እንዳንለው፤ የተደራሲ-እድሜገደብ ባይነግረንም እንደ ኃላፊነት ድንገት የተሰማው ዜጋአዊ (civil) ከፍተኛ ወሲብ-ቀስቃሽ እና ግልጥ ገጽዎቹ (obscene pages) ይገድቡናል። ስለእዚህ፤ ለልጅም ለአዋቂም የእማይሆን ሆኖ እናገኘዋለን።
ወደ ፈጽሞ ረብየለሽ ጭብጡ ፍተሻ እንሻገር። በጭብጥ፤ ከስነጥ. (ስነጥበብ) አላባአዊነቱ በዘለለ እንደ ዜጋ በአንድ ይዘት ላይ ያለው አቋሙን፤ ስነምግባርአዊ ስምጠቱን፤ የአተያይ አድማስ መጠኑን፣ ደራሲው ያስመለክትበታል። ከመዝናናት ጎን፤ ተደራሲዎችም እምንወርሰው አተያይ ስለእሚሆን የበለጠ በማጠንከር መመዘን እሚገባን ነው። የ አዙሪት ዘአልፋ ጭብጥ እንዴት ነው?
በጠቅላላው፤ በሁሉም ጎን፤ የወረቀቱን-ዋጋ አስብል ደረጃ ክሹፍ ፍሬ-ፈርስኪ፣ ታህታይ-ተርታመደዴ (sub-mediocre) የአመለካከት ከቶ ጎልማሳአዊነት የማያውቀው፣ ሌጣ-ብልህ፣ እና የሺህ እና ሺህዎች ዘመንዎች በፊት አቋም የያዘ አዳም ከገነት ሲባረር ቢያገኝ እሚተቸውን ጭርጭዝ-ጭብጥ-ጨባጭ ነው። በእርግጥ፤ የማብቂያውን ሴራ ላተኮረበት፤ ከፍተኛ የጭብጥ ዝቅጠቱን መታገስ ይከብዳል።
በአጭሩ፤ ዜጋዎች በሂደቱ እንዳይነኩ እና በፍፃሜው የኢትዮጵያን ንፅዉሳኔ (democracy) ለመገንባት እሚጣጣር ተቋም፤ በመጨረሻው ሴራ ግን የሀገር አገልጋዩን ግለሰብ ከስራ ሲያስቆም እሚያስመለክት ነው። ለሀገር እሚበጅ፤ በአነሰ ጥቅም እሚሰራውን ዜጋ መስዋእት ያድርገው ይለናል።
ይህን አይነት አንዱ ሌላውን እኔ እሻልሀለሁ እንዳሻኝ ላድርግህ ባይ መርኅ የጠፋ እንጂ የዘመንአዊው ዓለም አይሰኝም። ሀገር፤ አንድ ዜጋን በብዙ መስዋዕት ትጠብቀዋለች። የሀገርነት ፍፃሜው አንድ አስገዳጅ ዐዉታሩ ያ ነው። ያ የመጨረሻውን ዜጋ እእምንመለከትበት መንገድ ደግሞ እራስአችንን እምንመለከትበት ነው። ያ ከሆነ፤ አንዱንም መንካት አይገባንም።
ከግሉ እሚያጣርሰው ደግሞ እሚመክረን አንነካካ ሆኖ በመነካካት ማለቁ እና አንዱ እና ሌላውን እኩል መመልከት አለመቻሉ ነው። የተሻለ አማራጭን መመልከት አስገዳጅ ነው። ለሁሉም ረጂ መሆን እና የተሻለውን ስምጥ (ስርነቀል) መፍትሄ መፈለግ መልካም ነው። ያ ጎልማሳነትን ተርጓሚ ነው። በቀረ፤ እንደ እማያውጠነጥን ከላይ ከላይ ባሉ ገሀድዎች ምርመራ እምንጨልፍአቸው መፍትሄዎች እንደ አዙሪት ጽንሰሃሳብ እጅግ መደዴ ናቸው። አንክሮትአዊ አተያይ፤ የተሻለ የሁሉን ችግር አሳሽ እና ፈቺ እንጂ አንዱን ከሌላው ለማስበለጥ እሚኳትን አይሆንም።
ያን ማሠስ እና የተሻለ ጉዳይን ጨብጦ ማቀበል ቢችል እሚጠበቅ ነው። ዜጎችን በተራ ሚዛን ሰንፎ እና ወድቆ እንዲሁም ቸላ ብሎ በማበላለጥ ግን፤ ምንም ፍትህ፤ ምንም ዝማኔ የለም። ልብወለድ፤ ምርጡ፤ የስልጣኔ ሀሳብ ማንፀባረቂያው መሳሪያ፤ ሠርጎ ማሰብ አቅቶት ዝብ-አመለካከት ጨልፎ ሲተኩስብን፤ በእርግጥ ጎጂ ነው። የማህበረሰብ ጨለማን አያጠቃም። ብርሀን አይለኩስም። እረጂ አይሆንም። ያለውን ጨለማ ያስቀጥል አለ። አዲስ መሠረት አይጥልም። እኒህ ሁሉንም፤ አንድ ተራ ልብወለድ መሸከም እሚገባው መሰረትዎች ግን ናቸው።
በተለይ የምናብቴ ዘውግን (በመነካካትም ቢሆን) መርጦ እራሱን እሚያቀርብ ልብወለድ፤ የጨለማ መግፈፊያነትን ይቀዳጃል ተብሎ እሚታሰብ ነው። በገደብየለሽ ተምኔት እንዳሻው እሚዳክር ስለሆነ፤ ወደ ገሀዱ ሲመለስ ደግ ግኝት ሊያቀርብ ይገደዳል።
የጥበብ ምርት ዋጋን መመዘኛ አንድ ግንባርሥጋ ጥያቄ አለ። ለተግዳሮት፤ ማገዝ እና ልዩነት መፍጠር መቻል፤ እና አንዳች ዉብ ወይም ልዩ ነገር ጠቋሚነትን መጫወት፤ ይቻለዋል ወይ?
ያ ካልሆነ፤ ለምሳሌ አንድ ልብወለድን ለምን እንጽፍ ወይም አናነብብ አለን? ይህ ልብወለድ፤ በዘመኑ ሲታተም ያቀረበው ወቅትአዊ ፈገግታም በአንድ ተራ የመንገድ-ዳር እርምጃ ተራ ወሬ እሚቋጭ ነው። ከእዛ በላይ ያስፈልገው አለ። ዘላቂ ይውሰዱታ (takeaways) አይተርፈውም። ብስል ትርክት፤ ሴራ እና ጭብጥ ሊተላለፍ ይገባል። በቀረ፤ የጥበብ ምርቱ፤ ዘመንአዊ ኢላማውን አልመታም።
ሌላው የጭብጥ አንካሳነቱ በመሠረትአዊው የትልም አወቃቀሩ መሠረቱን መሳሳቱ እና አሁንም እንደለመደው ግሉንመጣረሱ ነው።
በሴራው መሰረት አንድ ህቡዕማህበር የእኛ ሀገር የብሔርአዊ ምርጫ ድምጽ ዉጤትዎች እንዲከበር ይታትራል። ምኑም አያገባንም። ድምፅ ግን ይከበር ባይ ድብቅ ተቋም ነው። ይህን በማያዛልቀው የደግ-አሳዳጅ አጭር ትልም ይጀምረዋል። ያም ሠፊ መወጠኛ (ሴት አፕ) እንዲሁም ስህተት ነበር። ምርጫ እሚያገባው ተቋም ሠላይዎችን በተጨማሪ ዋስነት (ከብሄርአዊ ደህንነት በተጨማሪ) ለሀገሩ መስራቱ ግራ ያጋባን አለ። ምርጫ ማስከበር ወይስ አንዳንዴ ሰላይዎችንም ማጋለጥ? አንድ ኢላማው ምርጫ ተብሎ ሌላ ቦታዎች መራወጡ ለልብወለዱ የሴራ ችግር ነው። ነገርግን ያ ብቻ አይደለም። ይህ እራሱ ነጥቡ ከሌላ ነጥቡ ይጣረስ አለ። ይህም ምርጫ እና ንጽውሳኔ የድብቅ ቡድን ጠላት መሆንአቸው ነው።
ሀገር ወደ ንቁ ንፅዉሳኔአዊ (democratic) ባህል እንድትገባ፤ ድብቅ ቡድን መመስረት አይረባትም። ሙሉበሙሉ ፍየል ወዲህ። ንፅዉሳኔ (democracy) ንቁ እና እልህአስጨራሽ ሁሉንአቀፍ ተሳትፎ ይጠይቃል። ድብቅ ማህበር ደግሞ ንጽውሳኔን በመርኅ ደረጃ እሚፃረር ነው። ድብቅ ቡድኑ ኦዲት መደረግ ስለእማይችል የማህበረሰብ አደጋ ነው። ለምሳሌ እንዳየንው ለምርጫ ድምጽ ማስከበር የተቋቋመ ድርጅት ወደ ደግ-አሳዳጅነት እሚገባ ከሆነ፤ ቀጣይስ? ምንም ማስረጃ ህዝብ እና ተቋምዎቹ ይዘው አይከታተሉትም። ዳግመኛም መርኁ ማንንም አንነካምን በመጨረሻ ያየንአቸው አማራጭዎች ሳሉ ትቶአቸው ሰውን ስራውን በታማኝነት ስለሠራ ለአደጋ አጋልጦ የተቋጨ ትርክት ነው። ሲጠቀለል፤ ድብቁ ቡድን ሁለቴ አልታመነም። መርማሪ ግን የለም። ያ እና ያ ብቻ ሳይሆን በተጨማሪ ፍልስፍናዎች መሰረት፤ ህቡዕማህበር በዘመንአዊ ሀገር እጅግ እሚከለከል እና ለንጽውሳኔም ጸር የሆነ ጉዳይ ነው። ሁለቱን መታረቅ እማይችሉ እሳት እና ጭድ ጉዳይዎች ማስታረቅ አይቻልም።
የ ዶናልድ ትራምፕ (ትንሹ) አልወርድም እና በዓለም የመጀመሪያው ሁለቴ በምክርቤት የተከሠሠ ሊቀመንበርነት እና ንቁው የአሜሪካአዊያን ትግል፤ የተገነባ ንፅዉሳኔን እንኳ እሚያሰራው ማንም ሳይሆን ገሀድአዊ ወጥ ትግል እንደሆነ ለሉል አሳይቷል።
ንፅዉሳኔ ባህል ነው እሚለንን የምሁር የንፅውሳኔ ሀሁ አስተያየት ሁሉ አንርሳ። ከግሪክ-ጥንቷ ጀምሮ ንጽውሳኔ የአኗኗር ዘዴ እንጂ ሌላ ምንም ያልሆነ ነው።
ንፅዉሳኔ ከቶ በህቡዕማህበር እንዲጠበቅ ትልም አይቀደድለትም። ንፅዉሳኔ ቶሎ እሚያጠፋው ዘወትር እሚቃወመው ነገር ቢኖር አንድም ይህ ቀንደኛ ጠላቱ ምስጢርአዊነትን ነው። እና፤ እማይገጣጠሙትን ለማዋድ ጥሮ በራሱ-እሚወድቅ ልብወለድ አዙሪት ያቀነባብራል። ጥንትአዊ ድሀ ጉዳይ!
ይህ ዉድቀት በእዚህ ዘመን መከሰቱ አይገርምም። የሀበሻ አኮብኳቢ የጥበብ ግዛት ከርሰምድር ከገባች እነሆ ግማሽ እድሜዘመን ተቆጠረ። ፀሐፊም ሆነ ተደራሲ፤ ቁምነገሯም ነጥፏል። ከእዚህ ሀገርአዊ ክስመት ጎን፤ ይህን እያወቅን የደፋብንን ሚዛኑን ዕዳ አናብዛበት።

ዳሩ፤ የሀበሻ ስነእናኪነጥበብ ብዙ ከእዚህ የተሻለ ጥረትዎችን ተንጠራርቶ እናያለን። የእነ በዓሉ ግርማ (የህሊና ደወል እና ከአድማስ ባሻገር)፤ ሀዲስ አለምአየሁ፤ ወዘተ. የተሻለ የህዝብ ንቃተህሊና አንሺ በጎን ደግሞ ያልከፋ ሴራ አስመልከተው አሉ። ከእዛ ቀጥሎ ዱላውን ተቀብሎ (መነሻአችን ላይ ልብወለዱን እንደጠቀስንው) መዘመን አስገዳጅ ነው። በእየሀያ አመቱ አካባቢ እጅግ ደምአፍሳሽ መንግስት ግልበጣ እና ሁሌም ቂጥቀርነት እና ከሁሉሀገር ከፊው ድህነት መዉጫው ዝማኔ ነው። ለእዛ ደግሞ፤ ቀለል አድርጎ እንደዋዛ በእነቀልቤሳ አስተምህሮት ለመማር መጣር ምርጡ የጥበብ ምክር መሆን አይችልም። አልወለድም፤ እንጉርጉሮ፤ ወዘተ. እሚሰኙ የቀኃሥ. ዘመን አካባቢ ስራዎች እንኳ ከእዚህ የተሻሉ ሆነው፤ ትልቁን እና ብቸኛውን ህዝብአዊ መንግስትነትን አቀንቃኝ ትውልድ ፈጥረዋል።
እንደሀገር ወዲያው ተዘቅጦ፤ ምህረትየለሽ ኦናነት ቢከብበንም፤ እንዲህ ያለ አፊያዥ ደረጃ ወደኋላ በራስእጅ መሽቀንጠር ግን ከቶ ዝቅተኛነት ነው።

የጭብጡን ጉዳይ ትንሽነቱን እንደእሚከተለው በቀረበ ውይይት እንቋጭ። አብሮ አንዳንድ ደግ ይዘት ባቀፈው የታፈኑ ቀልዶች እና ቁምነገሮች መጽሐፉ ላይ (2006)፣ አስፋው መኮንን፣ ያሣተመው አንዱ ቀልድ/ቁምነገር “የደከመው ባለስልጣን ማረፍ እንጂ አምባሳደር መሆን የለበትም” ከእሚለው ቀጥሎ፣ “የኦሪት አራዳ”፣ ባለው የአጭርአጭር መልእክቱም የ”አራዳ” አመለካከቱን ይገልጣል። እድል የለም። በቀጥታ በግጥሙ ማንበብ ወቅት የታየኝ የአራት ኪሎ አካባቢ ጫማ ጠራጊ የገጠመው ያክል ሆኖ ነው። ሴትዎች እና ወንዶች በጆሊ ሲዝናኑ እየተመለከቱ ጥቃቅን ነገርዎችን ይሸጡልአቸው አሉ እና እነእሱ እሚያወሩት ግጥም ይመስል አለ። ብቻ፣ እንደእዛ አራዳ-ግጥም፣ እንኳ ያረጀ የአመለካከት ዓይነት መሸከም ያልቻለ አስቸጋሪ ጉዞ የጨበጠ ትርክት ነው። ተዘንግተን እንደ እማይፈለግ ፍጥረት ተንቀን ተወልደን እንደ እድል በእሚል የሀበሻ ሰብእአዊነት መርኅ አድገን እምንንከራተት ህዝብዎች፣ ጥቂት ከመንገድ ዳር ወሬ የተንፏቀቀ ብስለትን ማቅረብ ይገባን አለ።
በእየቀኑ መሀከልአችን የእሚሽከረከር ችግርን ከተርታነት ተንፋቅቆ በእማይሽከረከር ዴርቶጋዳአዊ ሰነፍ ፈውስ ለመሥጠት መሞከር ድህረ-ኦሪት የተቀረቀረ፤ የእሳትዳር ተረት መሰል ድርሰት መሆን ነው። ድህረ-አብርኆት (post enlightment) ዉስጥ ለውጥ ፈጣሪ ትርክት ለመተረክ ተጣጥሮ እንኳ ብዙ የወደቀ ሳለ፣ ከእዛ ባፈገፈገ ድንበር የተደበቀ ስነጥበብ ልናገር ማለት ከኋላቀርነት ወደኋላ ጎታች ነው።

በእርግጥ፤ አዙሪት እሚለው ጽንሰሃሳብ ቀላል አይደለም። ገሀድ ችግርአችን ነው። ክፉ ጠላትአችን። ያም በደፈናው ኋላቀርነት ማለት ነው። ግን፤ ይህን ለመገንዘብ እና የአዙሪትአችንን የበዛ ክፋቱን ለማወቅ በእራሱ ይህ መጽሐፉ (በእዚህ ይዘቱ) መኖሩ አንድ ማስረጃ ነው። መፍትሄአችን ፍቱን (panacea) እንጂ ተራ አንድ የታየንን ችግር የማስወገድ ፍልስፍና መሆን የለበትም። ስርነቀል ከአልሆነ መፍትሄ ፍቱን አይደለም። የአዙሪት ዘአልፋ ሙከራ ደግሞ ከደፈና አንዳንድ ኢልብወለድአዊ ወሬው በቀረ፤ ገና የመፍትሄ ፍለጋ መሠረትን ያልነካ እና ከላይከላይ የተጨለፈ ነው። ወደቤት ወስደን እምናብሰለስለውን ለልጅልጅ እምንናወርሰውን ስነስርአት ለማበጀት እሚያግዝ መፍትሄ ያልጠቆመን በመሆኑ ከቶ አጋዥ መሆን እማይችለው ሆኖ እሚቋጭ ነው።

ቀጥለን ምንም በጥቂቱ ቢበረታበት የሰነፈብአቸውን ጅሌትዎቹን (goofs) እንመልከት። አንድ ደገኛ ጅሌት (goof) ብናነሣ፣ የ 2005 ዓም ልብወለዱ፤ በ2004 ክረምት ያረፉትን የቀድሞ ጠሚ. መለስ ዜናአዊ ስምን ጠርቶ ባለፈው ሳምንት በመስኮተድምጽ (radio) ሰማኋቸው ብሎ ገጸባህሪውን ያናግራቸዋል። ከምርጫ ቀድመው ከአረፉ ቆይቶ የተመረተ ቢሆንም፤ ስለምርጫ ግን ያስሠብክአቸው አለ።
ሁለተኛው የፍሬነገር ጅሌት ነው። ገ.17 ላይ መንግስተ-ኢህአዴግ. ከቻይና ኮረጁ ይል አለ። በእርግጥ ግን ለማንኛው ስነውሳኔኛ (politician) ኢህአዴግ እና የቻይና ኮሚኒስት ድርጅተደ ባልደረባዎች እንጂ፣ ምንም ያልተኮራረጁ ናቸው። በቻይና በአንዳንድ ጉዳይዎቹ የሠመረ ማህበረሰብአዊት ድርጅት ሲኖር ጥብቅ እና ታታሪ በእራሱ መንገድ እየተጓዘ ቻይናን ከመሬት ወደ ከሁሉ ሀገር በላጭ ሠማይ ያደረሰ ነው። ኢህአዴግ. ሀገር በዝባዥ፣ ግራ የተጋባ፣ ከፋፋይ (ገ.18 እንዳለው ቤተሰብ ጭምር ሰንጣቂ ዘር-አጉዪ)፣ ሙሰኛዎችን እንደቻይና በስቅላት ከመቅጣት በስልጣን ማሻሻል እሚያሸጋሽግ፣ የልማትአዊ መንግስት ብሎ ሌላ መንግስት ኢልማትአዊ ይመስል ድንግርግሩ የወጣበት፣ ምኑም ሆነ ምኑ ከብዙ መንገድዎች አንፃር ቻይናን ያልተመለከተ መንግስት ነው። ይህን መሠል ጉዳይዎች አጥርቶ መመልከት ከደራሲ እሚጠበቅ ነው። የተባለውን ሰምቶ እሚደግም – ሀቁን መርማሪ ያልሆነ ጋዜጠኛም ሆነ ስነውሳኔኛ መሆኑ በጥራቱ ላይ እሚያጠያይቅ ነው።
ሀገርአዊ የጥበብ ጉዳይ
አንድ ነገርን በአጋጣሚ ቀጥረን እንወያይ። በጠቅላላ፤ ይህ ተዋዳጅ ሀያሲ እሚያምነው የሀበሻ ስነእናኪነ ጉዳይዎች መሀል አንድ ነጥብ አለ። የሀገርአችን ጥበብ ምርት፣ ከሌላው የአደገ ሀገር ጥበብ መለየት ለብአቸው አመክዮዎች አሉት። እኛ ገና በዘመነ መንገድ አልተመሰረትንም። የድሀድሀም ነን። ከቶ ያልሰለጠንንም ሉልአዊ ተመጽዋች ነን። ከሆነ፤ ጥበብን አመረትን ካልን መግለጥ ያለበት ሀቅ ያንን እንደሆነው ሌላ መሆን የለበትም። ያ አንድ ነው። ዋናው ሌላው ደግሞ፤ ገና ያልመሰረትንአቸውን ዋናጅረት አመለካከትዎችም በእሚገባ መመስረት ይገባናል። ለምሳሌ፤ ገና የእኛ አኗኗር ጭብጥ ሁሉ በጥበብአችን ሽፋን አላገኘም። ብዙ የመተባበር፣ የመስራት፣ ራስንየመቻል እና ማበልፀግ፣ ከወደቁበት ተነስቶ ዳግማሸነፍ፣ ብሄርአዊነት፣ ወዘተ. ብሉይ (classic) እምንልአቸው ስራዎችን አላመረትንም።
በእነዚህ ሀገርአዊ አረንቋዎችአችን አነሳሽ እና አንፋሽ (inspiring) ልኮት (reference)፣ ዘመንአይሽሬ ስራዎች ማከማቸት ይጠብቁናል።
በእዚህ ገሀድ ሀገርአዊ የጥበብ ክፍተት መሀከል፣ በቂ የምርት ክምችት በሌለበት፣ የጥበብ ምርትዎች ዝባዝንኬ መዘብዘብ የለብአቸውም። ይህን ደጋፊ ሁለተኛ ችግር አለ። የማንበብ እና ምርት በገበያ አሽከርክሮ የማቅረብ ባህሉ እጅግ ትነሽ ነው። ተደራሲነት እጅግ ኋላቀር ነው። ጊዜማሳለፊያ እንጂ ቁምነገር በጥበብ እንደሌለ በአልሰለጠነው ህዝብአችን ይገመታል።
ስለእዚህ፣ ይህን ቀይረን እንደ ቀደመ ነቃ እንዳለው እና እነ ኦሮማይ፣ የህሊናደወል፣ ፍቅር እስከመቃብር ወዘተ. በማንበብ ስለጋራ ችግር ይነሳሣ እና ሀሳብ ይለዋወጥ እንደነበረው ትውልድ፣ የሀበሻ የአሁን ኪነእናስነም እንዲሁ መበርታት እና ትውልዱን መምራት ይገባዋል። እንጂ፣ በመቃረን፣ ያልተማረው ኢስልጡን መንግስትአችንን በመደገፍ ትውልድ እማያነቃ እና የጥበብን አቅም እሚያስረሳውን ባዶ ዋጋ ያለው ምርት እየሞጀሩ የተገደበውን አንባቢነት እና ገበያ መጋራት ይልቁንም እንዳሳዛኙ እውነት ያልበራ ትውልድ መፍጠር እና መቆጣጠር አይገባም።
ጥበብ አቅሟ ከፍተኛ ነው። ለቱልቱልቴ እንኳ ከፍተኛ አገልግሎት ታቀርባለች። እንዲሁ፤ ለዝማኔ፣ አብርኆት እና ማዕዶት እጅግ አኩሪ መሪ ሚና ማገልገል እምትችለው ነች።
ታዲያ፣ በወዳደቁ እና ርካሽ ዋጋ የያዙ ምርትዎች ንቃተህሊናን ማበላሸት የትውልዱ ታሪክን ማቆሸሽ ነው።

መደምደሚያ


ያልሠመጠ እና ናሙናአዊ አሠሳአችንን ለመጠቅለል፤ በእሚል አሁን እንግታ። አወዳደቅዎቹን መዘርዘሩን ቋርጥ። መጽሐፉ በደፈናው ደግ አይደለም። ልብወለዱ እሚነግረው ስለሌለው እንኳን ላቋረጠው ታግሶ ለጨረሰውም ማበሣጨት እሚችል – የክንዱን ዝውውር ያላደመጠ – ተራደፋር ይዘትአዊ ምርጫን የተሸከመ ነው።
በእዛ ዙሪያው ከተማማርን በኋላ እነሆ ወደ ተስፋ እንመለስ። ደራሲው የመፃፍ አቅሙን ደግ ሴራ መጎንጎን ለምዶ እና የስልጣኔ አካል የሆነ ጭብጥ ጨብጦ እንዲመለስበት ይመከራል። ቀላል ስልተ አተራረኩ፤ ቅልል እሚል እራሱን የመግለጥ ስኬቱ፤ ቀላል የቋንቋ (አማርኛ) አቀጣጠሩ፤ በትርክት አቀነባበር ዙሪያ ያለው ተስፋው፤ በተለይ በቀለለ መንገድ ትርክት ለመካብ ወይም መቅዳት እሚያደርገው ትትረቱ፤ የአርትዖት እና ትየባ ጭንቀቱ፤ በአስገራሚ ሁኔታ በቅርቡ ከእምንመለከትአቸው አማርኛ አፃፃፍዎች ደግ እሚያስብሉት ናቸው። ዳሩ ለተደራሲ ይህ ሁሉ ተስፋ ምኑ ነው? የተማረ መዝናኛነት አስፈላጊ ነው። ስለእዚህ፤ በተነሱት ችግርዎች መጠንከር ከቻለ እነእዚህ ነጥብዎች ጥራትዎቹን እሚያግዙት ሆነው ያሻሽሉታል።
የበላይ ምርት የከፉ አፍጢም አወዳደቅዎቹ ከቶ ለመቆም ቢያስቸግሩም፤ የመተረክ፣ ማቅለል፣ ማቀነባበር፣ አቅሙ እንዲጎለብት ማሳሠቡ እና አግጣጫ መጠቆሙ ስለእዚህ ከሁሉ ነጥብ በላይ የእዚህ ፅሑፍ ኢላማው ነው። የምርአዊነትን ተላብሶ፣ በጥበብ አቅም ተማምኖ፣ ጠቃሚ እና ልዩነትፈጣሪ ጭብጥ ከሴራ አዳብሎ፤ ይህን የትርክት አቅም ማፅደቅ ከቻለ፤ ደህና ችግኝ ያለው ደራሲ ነው። ነገን እንደእሚያስበልጥ ተዋዳጅ ሂስ (fan’s critic) ግን፣ ጀርባ-ቸብቸብታ ለበጎ ጎንዎቹ እንዲሸልም ተፈቅዶለት አለ፨

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s