Categories
መልካም ጥበብዎች Fine Arts

የዲናው መንግሥቱ መቀደሻ (ዴቢው) ልብወለድ “አምላክ እሚሰጣቸው ዉብ ነገሮች” ወይም “የአብዮቱ ልጆች”፣ እጅግ ጭፍግግ ትርክት፣ እጅግ አስቂኝ፣ ዉቡን ነገር በመቀነስ የጨከነ፣ ግን እጅግ በደጉ እምቅ

ዲናው መንግስቱ በተዋዳጅ።

ፅሑፍ፦ የተዋዳጅ ሂስ (ፋን ሪቪው)፤ ደራሲ፦ ዲናው መንግስቱ ፤ እርዕሥ፦ Children of the Revolution በአሜሪካ ግን The Beautiful Things that Heaven Bears ፤ እትመት 2007 እኤአ.፤ 178 ገፆች፤


ቢንያም ኃይለመስቀል ኪዳኔ
2011 እና 2013 ዓም፣ አዲስአበባ-ወ-ወልቂጤ፨


“ከክቡ የጮራ ቀዳዳ፣ እየወጡ አየሁ ሲገለጡ፤
አንዳንድ ዉብ ነገሮች፣ ከአምላክ የእሚሠጡ፤
እና ወደወጣንበት (ዳግ)እንደገና፣ ክዋክብት ወጡ!”

[ዳንቴ አሊጌሪ፣ በ ልብወለዱ ተቀንጭቦ እንደተጠቀሰው፣ ትርጉም በተዋዳጁ]

ሞላጎደል፣ መቶበመቶ እሚያዝናና፣ መልእክታም፣ አስተኔ-ደንበኛ-ጨለምተኛ፣ ራሮት-ጠል ትራጄዲ አሀድ (ዩኒት/ፒስ)። ከማህበረሰብ እና ግለሠብ አንፃርዎች ደግ-ተቺ ይዘት። ጨለምተኛ ትርክቱ፣ የንትብ-ኑሮ ስእል ነው። ከአፈታት ብቻ፣ ብርሀንአማ-ኑሮ ሰባኪ ነው። ክልክል ጎዳናዎችን መጠቆም ስለተፈቀዱት ማሣበቅ በእሚሆንበት አጋጣሚ። ይህን ለመምዘዝ፣ የአንባቢው ፍልፈልአዊ አቅም ይወስነዋል። ወደዉስጡ እንግባ እና፤ ትርክቱን እናብራራ። ቀጥለን በገሀድ (ወይም እማሬ) ልለግስ እሚለንን አዎንታአዊ መልእክቶቹን እንይለት።
ከማህበረሰብ አባልነት ሲያግድ፣ በባይተዋርነት ጠቅልሎ ሲሠርቅ፣ በመነጠል ጅራፍ ሲገርፍ፣ የስደትን ቀዝቃዛ እና የለሽ-ራሮት ጎን ያሣያል። ያ መስመር፣ ትርክት የቆመበት አከርካሪቱ ነው። ወዲያው፣ ለዛ ቅዝቃዜ መልስ አበጀ። ዳሩ፣ ያ የመጨረሻ-አማራጭ ነው። እንደልብ አያሞቅም። ጭራሽ አሳዛኝ ነው። እንደ መቋቋሚያ እንጂ እንደመፍትሄ እሚነገር የለም።
ስለእዚህ ከጭብጥ-ልጓሙሟሞቹ ከሁሉ ጉልኾቹ፣ ምናባቱ ባለህ ህይወት ተደሠታ፣ ከእይታ ተገልለህ ለመኖር ብትሞክርስ፣ – እና ሦስተኛው (ፍካሬአዊ) ዐብይ ይዉሰዱታው (ቴክኧዌይ) – ጨለማውን አኗኗር በረዥሙ ሥሰብክልህ፣ በሂደቱ ብርሀን ከታየህ ትሞክራለህ ብዬ ነው፣ ይመስላሉ። የመጨረሻውን ለማፍታታት፣ በቀጥታ እንደ መነሻ-ደረጃ ተደራሲ ማንበቡ ብቻ በቂ አይደለም። እንዳልንው የመተርጎም ስንዝር ፈቅ-ያለ አቅም ያሻል።
የልብወለዱ ትርክት። የስደት ጉስቁልና ያወላጨመባቸውን ህይወት፣ ሠፋ እስጢፋኖስ፣ እና ሁለት ጓደኞቹ – ጆሴፍ ካሃንጊ እና ኬኔት – በተመሳሳይ ይጎነጫሉ። ተዓግ. (የተባበሩት አሜሪካ ግዛትዎች/ዩኤስኤ) በስደተኛነት ከደረሱ አስራሰባት አመቶች በኋላ ሁሉ፣ ያው-ተስፋቢስ እንደሆኑ መታገል ሲቀጥሉ ልብወለዱ እንኳ እሚተዋቸው ዋና ገፀባህሪዎች ናቸው። ትርክቱ መቼቱን ፈነካክቶ በመዘበራረቅ ሲራመድ፣ በእየኪራይ ቤቶቻቸው ያሉት ትመ. (ትእይንተመስኮት/ቲቪ) እና አልጋዎቻቸው አንጡራዎቻቸው ሆነው ሲኖሩም ያለቤተሰብ ምስረታ ጎልማሳነትን ይቀራረባሉ። በ 1970 ዓም. አካባቢ በምድረ-ዕድል ሲደርሡስ? በ ካፒቶል ሆቴል የእንግዳዎች-እቃ-ተንከባካቢነት (ቤልሆፕ) ሲሠሩ ተዋወቁ። እሚዋደዱ እና እንደአሜሪካአዊያን ሰርቶ ታላቅ ለመሆን ለጥጠው እሚያልሙ ነበሩ። ዳሩ፣ ሦስት አመቶች ሰርቶ ሠፋ ብዝበዛ አጥንቱ ድረስ ተሰማው። እንጂ እድገት እንደሌለ ከበርቴአዊ (ካፒታሊስት) ስርኣቱ መጥጦት ተንገፍግፎ ተማረ። ካረፈበት አቻ-ድሀው የአጎቱ የሀበሻዎች ድሀ ሰፈር (ሜሪላንድ) ኪራይቤት እና የታከተው ስራው ይለቅቃል። ኑሮው ከድካም በቀር ለውጥ አልቸረውም እና። አጎቱ ለራሱ የተሠደደው፣ በቀኃሥ. (ቀዳምአዊ ኃይለ ሥላሴ) አዲስአበባ ስኬታማ ጠበቃ እና የልዑልዎች ጓደኛ ሳለ ከደርግ አምልጦ ነው። ተስፋ ቸሮ እንዲማር ቢያደርገውም ሠፋ ሊለየው መረጠ። ሁለቱ ጓደኞቹ ግን “የአሜሪካ ህልም” ን መኖር ተስፋ እንዳደረጉ ለመታገል አልሰነፉም። ተምረው ዲግሪዎችን ማካበት፣ መልካም ተቀጣሪ መሆን ከእዛ ሀብትን ማካበት አስምረው እንዳቀዱ፣ ከእሱ በመነጠል ይቀጥላሉ።
ወደ ጨረጨዘ የዲሲ.-ጠርዝ – ሎጋን ሰርክል – ዉስጥ ከጥቁሮች እና ድሀዎች መሀከል ለመኖር ሠፋ አባቱ ሲገደልበት ደርግን አምልጦ በእግሮች ኬንያ ደርሦ ዲሲ ከገባ በኋላ ወደብቸኛነት ተዛወረ። ሱቅ እንዲከፍት ኬኔት ባመጣው ሀሳብ ትንሽ ንግድ ጀመረ። ጆጆ ወደፊት የሱቅ ንግድ-ሰንሠለት (ፍራንቻይዝ) እና ከበርቴነትን ታገኛለህ ብሎ በቀኝአዊ አተያዩ ገፍቶ ችርቻሮዋ ተጀመረች። ብዙ ሳይቆይ፣ በመሀንዲስነቱ ተቀጥሮ ለሆነ ድርጅት ሊሰራ ኬኔት ጥቂት በተሻለ መንገድ ወጣ። ናይሮቢ ተመልሦ ትልልቅ ፎቆች መገንባት ሁሉ እሚያልም ሆነ። ጆጆ ኮሎኒያል ግሪል እሚሰኝ ምግብቤት ለማስተናገድ እንዲሁ ትንሽቆይቶ ተዛወረ።
ኑሮ ግን በቅጡ አልተለወጠም። እዛ ከደረሱ አስራሰባት አመትዎች አካባቢ ቆይቶ ግን አንድ ለውጥ በሠፋ ኑሮ መጣ። በድሀዎቹ መንደር ጁዲት – “ባለሴት ታዳጊልጅ ነጭ፣ ወጣት፣ እናት – “የሠፋ ጎረቤት ሆና ያሳደሰችው ቅንጡ ልእለቤት (ማንሽን) ገባች። ወዲያው ተቀራረቡ። ናኦሚ፣ ትንሽ-ልጇም፣ በጣም ወደደችው። ተቀራርበው ወሮችን ገፉ። ዳሩ በዓለ ገና ሲደርስ እንደዘበት ጥለውት ሄዱ።
የትርክቱ ሂደት ወደመቋጫው ያኔ ያዘምማል። የሁሉም ስነምጣኔአዊ ክሽፈት ጡዘትአዊ-ማረጋገጫ ላይ ይደርሳል። አብሮ ወይም ተከትሎ ግን በላጭ ከፊው ሀቅ ያገጣል። ባይተዋርነት እሚገልጠው የኑሮ ኦናነትአቸው።
ዉጥንቅጡ ሲራወጥ፣ ሠፋ ሱቁ የኪራይ ዉዝፍ በዝቶበት እንዲለቅቅ ማስጠንቀቂያ ተሰጠው። መክፈል አቃተው። ጆጆም በቅፅአዊ (ፎርማል) ትምህርት ተምሮ፣ በግሉም አጥንቶ ተስፋ እሚያደርገውን ለውጥ ሲጠባበቅ ምንም አጥቶ ሠለቸ። ሂደት-በሂደት በመራሩ ኑሮ ተሸንፎ እጅሰጥቶ አስተናጋጅነቱ ሳይማርከው መስራቱን ብቻ አፀደቀ። ለምዶ በግድየለሽነት መኖር ቀጠለ፤ መለወጥ እንደማይችል መንፈሱ ተሰብሮ ለመደ። ሠፋ ብድር ሊጠይቀው እማይችል ሆነ።
ከሦስቱም የተሻለው ኬኔት፣ ያፈጀ ልባሽ መኪና ከመግዛቱ በዘለለ በተመሳሳይ ለውጥ የለውም። የጠነሠሰው የአሜሪካ ህልም ድፍድፍ ሆኖ ቀረ። በአለቃዎቹ እማይታሰብለት ተበዝባዥ እንደሆነ ቀጠለ። ለገናዕለት ለብቻው ቀኑንበሙሉ ሥራ እንዲገባ ተደርጎ ከጓደኞቹ ባሪያ ነህ ሁሉ ተባለ። በመራር መልስ ተነጋገራቸው። አንድሺህ ዶላሮች ማጠራቀሙን እና ሱፍ ከመኪና ጋር እንዳካበተ ስለእዚህ ከእነሱ እንደሚሻል አምባረቀ። የእነሱ ሁኔታ ያነሰ እንደሆነ ነገረን። የተሻለነቱን ሲገልጥ ሁለቱ በአንፃርአዊነት ኦና ነበሩ።
በርግጥ ብቸኛ ሲሆን ገናን ሱቅ ከፍቶ ሠፋም ነግዷል። በዓሉ አልፎ፣ ጁዲት ልጇን እህቷ ጋር በሄደችበት ኮኔክቲከት ትታት ከተለያየችው የልጇ አባት ዕውቁ የሞሪሸስ ፕሮፌሰር አያድ ጋር መጥታ ቤቷ ገባች። እጅግ ተቀራርበው ሳለ ድንገት ያን ማድረጓ ሠፋን አስከፋው።
የትርክቱ ጡዘት እሚፈለፈለው የሎጋን ሰርክል መንደሩ ለለውጥ ድሀዎቹን ሲያፈናቅል ነው። የጓደኞቹ ኑሮን ትርክቱ በእዛ ፈፅሞ ወደ ሠፋ ዞረ። እሱም፣ አጎቱ ጋር ለድጋፍ ወይም ብድር እንኳ ቢሄድ አጎቱም እንደቀሩት ምንም ያልተለወጠ ድሀ እና አንድሺህ ዶላሮች ብቸኛ ሁሌም እሚቆጥበው መዳፍገንዘቡ (ካሽ) ነበር። ለመስረቅ እና ዕዳ መክፈል ወይም ሀገርቤት ወደእናት እና ታናሽወንድሙ ለመብረር አሰበ። ግን ተወው።
ጁዲት ከአያድ የለየለት ጠብ ዉስጥ ሰመጠች። በጎን መንደሩን ተናድደው የለቀቁ ሰዎች በሰላም አሌዱም። ከመሀከላቸው አንዱ ተስፋ የቆረጠ የመልሶማጥቃቱን ጥፋት ጀመረ። ህንፃዎች በደፈጣ ተመቱ። በዋናነት የጁዲትን ቤት በሌለችበት ለኩሶ አነደደው። እሷም ተስፋ ቆርጣ ለአዲስ ኑሮ ሠፋን ጥላው ከናኦሚ እንዲፃፃፍ አድርጋው ግንኙነቱ ሳይገፋ አልቆ ተለያዩ።
ጭፍግግ ያለ ትርክቱ እጅግ አሳዛኝ ሆኖ ተቋጨ። ሠፋ ጁዲትን ለመጨረሻጊዜ ሲሸኛት፣ ኑሮውን ፍቺ ሰጥቶ በቀናነት ሲመለከተው እና ቢያንስ ያልፈረሰ ሱቅ ስላለው ለመደሠት እና ተደብቆ በማንበብ እስኪሞት ሊኖር መወሰኑን ሲያፀና ያልቃል።

ሁሉም አሳዛኝ ነው። ደካማው ኑሮ አልተቀየረም። ስደተኛነቱ በአዲሱ ሀገር አላሳካላቸውም። ወይም በእየቤት ሀገርአቸው መመለስ እና መኖር ምንም አልሆነላቸውም። በሁለት ስልጣኔዎች መሀከል ሁለት እግሮች ሠቅለው ወደአንዱ መድረስ ሲያቅታቸው በጨከነ ትረካው አሳየን። እውነት ሬት ሆነች።
ይሄ – በተለይ ከሀበሻ ወደአሜሪካ ተሳካ የስደት ልብወለድ አንፃር – ዕዉቅ የአማርኛ ልብወለድ ምስያ አለው። የህግ መምህር፣ ጠበቃ፣ ደራሲ እና ፖለቲካ ተሟጋቹ ሙሉጌታ አረጋዊ (ማረግአዊ) ዲቪ ሎተሪ (1997 ዓም.)፣ ተቀራራቢ ጭምቅ ትልም አለው። በ ዲቪ ሎተሪ የሀበሻዎች ወደአሜሪካ ስደት ቀዝቃዛ ፍፃሜ ሲያገኝ ልብተሰብረን አየን። ከአዲስአበባ ወደአሜሪካ ለመድረስ እሚደረጉ የፍልሰት ጥረቶች ክብር ሲያጎድፉ እና ጨካኝ አሜሪካ ስታገኛቸው እንጂ እንደታሰበው አሜሪካ የገነት ምድር ስትሆን አላሳየንም። ከሁሉ ይልቅ ግን ጭፍግግ የትርክቶቻቸው ጡዘትዎች አንድ ናቸው ማለት ይቀላል። የስኬት ፍለጋው መዉደቅ፣ ወንጀሉ፣ ህግዘብ፣ እና እስራት ትርክቶቹ፣ በሁለቱም አንድ ሆኖ ያልቃል። የበለጠ በአስገራሚ ሁኔታ፣ ተመሳሣይ ቦታ እና ድባብ ላይ እሚስሏቸው መቋጫዎች የበለጠ ያዝ-ቆንጠጥ እሚያደርገን ነው።
እና፣ ወደ ዲናው መንግስቱ ብቻ ስንመለስ። ከመከራ በኋላ ከአምላክ እሚሰጡ ዉብ ነገሮችን ሠፋም ሆነ ሌሎቹ ስደተኛዎች አላገኙትም። ሲፈፀም ቀኝ-ተመልካች ልሁን ቢልም፣ በእርግጥ አቻ ቀናአዊ ፍፃሜ ስላላየን አምላክ እሚሰጠውን ዉብ ነገር አናይም። ያ ፍልቅልቅ እና ተስፋ ያለው ኑሮ ነው እና።
ስደት ሁሌ ይህ አይደለም። ስኬትም አለው። ዉድቀትም አለው። ትርክቱ የጨለመውን ማስመልከቱ ምርጫው ሆኖ እንዳለ፣ ስንጀምር እንዳልንው ደግ ክፍል በተጓዳኙ እይታ አብሮም አለው። ከነገረን ጭለማ ትርክት ተቃራኒውን በብልሀት እንድናስተውል እሚመክረን ነው። ከጦፈ አፈጋጊነቱ ቀጥሎ፣ ያ ዕንቁው ነው። በእከሊት-ተቀጣ ቅጥ፣ ማለትም በታሳቢነት፣ መልካሙን ነገር ሲነግረን ተራምዷል። ደራሲው ያንን ማየት የኛ ፋንታ እንዲሆን ለማድረግ ብዙ ስለእሚጥር ልብወለዱም አልሰነፈም።
ከአድራጎቶቻቸው፣ ካልከወኗቸውም ጭምር፣ ገፀባህሪዎቹ ብዙ እሚሰብኩት በርግጥም አለ። ወደቤተሰብ ማተኮር፣ ለራስ ክብር መስጠት፣ ወዘተ. እንድናስብ፣ ገሀድአማአዊ (ፕራግማቲክ) እንድንሆን፣ ባለመምከር ይመክረናል። እንዳልንው ያ ትልቁ ይዉሰዱታ ነው።
ከእማይነግረን ያ ትልቅ ስጦታው ቀጥሎ እሚነግረን ማየት ደግሞ ቀጣዩ ነጥብ ነው። የእሚታቀድ ስኬት ካልተሳካ፣ በቀና አመለካከት ያለውን እንድንቀበል በመንገር ይነግረናል። በግልጥ ከተሰበከው ጭብጥ አንዱ በትንሹ መመኘት እና በትህትና መኖር እሚሉት ናቸው። በደግ መጠን ዋጋ ያላቸው የመልካም ምክር እጭቆቹ ናቸው። እንደተገለጠው የመልስምት እንጂ ቅድመንቃትአዊ መድሀኒትዎች ባይሆኑም አሁንም የለሽምትክ ፈርጥ ናቸው። ምክሮቹ ደግ አቅም እና አሳማኝነት ይዘው ተገልጠዋል።

ልብወለዱ ላይ አነስ ያለ ማስታወሻን እና የምርአዊ የሆነ ትልቅ ነጥቡን ማንሳት ይቻላል። አንደኛው አነስ ያለው ነጥብ ነው። ልብወለዱ ጨለማነቱን ምርጫው ብለን ብንተወውም፣ ስደት ሁሌ ያንን ግን አይደለም እሚለው ነው። አምላክ እሚሰጠው ውብ ነገር መቼም ለማንም ቋሚ እድል ሆኖ አለ። እንደ ሠፋ በሁለት ዓለምዎች መሀከል የተያዘ፣ አንዱን አሣክቶ እስኪያበለፅግ ደበቅ ማለት ይሻ ይሆናል። እንጂ፣ አንዱን ዓለም ተምሮ በጨረሠ ወቅት፣ ያ ባይተዋርነቱ እሚሠበርለት ነው።
መማር እና መማር እያሉ፣ ተደብቆ መኖርን ብቻ አትግቶ ማጠንጠኑ የበዛ ፀሊምነቱ ነው። ጊዜን መካድ አይቻልም። ጊዜ ፈዋሽ ነው። ካልተመለሠ፤ በሂደት ስደተኛ፣ ባለበት ለማጅ ነው። እረዥ እሚጓዝም ደራሽ ነው። ዕዉቁ ሎንግ-ማርች በአንድ እርምጃ እንደተጀመረው፣ በጊዜ ሁሉም ይፈፀማል። በጊዜ እማይስተካከል ወደመልካምነት እማይጓዝ የለም።
የእነ ሠፋ ከስነምጣኔ ነፃነት መክሸፍ አብሮም ባይተዋርነት እና የስብእና ቅዝቃዜ ማግኘትአቸው አብዝቶ የከበደ ደመና ሆነ። ሠፋ እና ጓደኞቹ በጊዜአቸው ሄደው-ሄደው አልታከሙም፣ አልተስተካከሉም። ተንኮትኩተው የተሠባበሩ መሆናቸውን መረዳታቸውን ብቻ ይነገረናል።
የአሜሪካ አታሚዎቹ አስገድደው እርእሱን ከስነዉሳኔ እማይያያዝ አድርግልን በማለት፤ ኢትዮ-አሜሪካዊ ደራሲውን ስላሉት፤ ከአምላክ እሚሰጡ ዉብ ነገሮች ማለቱ እዚህ ጋር ቢነሳ ያግዛል። በላጭ ዉበት በእዛ እርእስ አለ። ግን፤ በእርእሱ የግዴታ ለውጥ ተከወነ እንጂ ቀና አተያይ በይዘቱ እንደሌለ ያሳየናል። ዉቡ ነገርን ትርክቱ ክዶታል። ማጥለያው፤ ቢያንስ ቀንሶታል ነው።
ይህን ሰፊ የእዉነትአዊነት ኋኝነትአዊነት (ፖሲቢሊቲ ኦፍ ሪያሊቲ) የሠፋው ትርክት ሊጓዝበት አይፈልግም። ከቶ ለጭጋጉ ትጋትአዊነቱን (ኮሚትመንት) ይሰጣል። ስለእዚህ እጅግ ጨለማ ወረሠው። አላማዬ በእድሜዘመኔ ተደብቄ በንባብ መኖር ነው ሲል፣ መራራ አተያየቱ በዛ-በዛ ብሎ ኢእዉነትአዊ (ኧንሪያሊስቲክ) ኢኋኝነትአዊነቱን ሲመርጥ እምናይበት ነው። ያንን ምርጫው ብለን ስንቀበል፣ ገሀዱ ግን ቀኝም እንዳለው ማስታወስ ብቻ በቂ ነው። ነጥቡ ያ ነው። በመጨረሻ ሞኖሎጉ ግን መለያየቱን ቀና አርጌ ልመልከተው አርፌ ልደሰት ማለቱ እንደ ቀና እንይ እሚገለጥ አይደለም። ያ የመጨረሻው ምክር እንጂ፣ እዉነቱ እራሱ ቀኝ መስመር ሊገባ እሚችልበት እና ዉቡ የአምላክ ስጦታ በብዙዎች እሚታፈስ ነው። ደራሲውን ጭምር፣ ከኢትዮጵያ የተሰደዱ በተንገዳገደ ተርታ ሱቅ እና ባይተዋርነት ወይም አቻ ወይም ከፊ ማጣት ያልቀሩ ብዙዎች አሉ። ዲናው እራሱ የተከበረ፣ የታፈረ፣ ተሰሚ፣ ስኬትአማ፣ የዩንቨርስቲ መምህር፣ እና የቤተሰብ ሰው የሆነው በሦስት አመቱ ከሸገር ተሰድዶ ነው። ሁሉን ትቶ፣ አብዮት ናፋቂዎች ስደተኞችም ሆኑ ፍልሰተኞች፣ ከጨለማው ጀርባ ብርሀን ቢያንስ በግል እና ቤተሰብ ህይወት ያዩ ናቸው። ትርክቱ፣ ሌላውን ጎን ስለእዚህ በትጋት መመልከት አብዝቷል።

ወደዋናው አንድ ተጨማሪ ዉይይቱ እንምጣ። አግጥጦ ስላለ ግድ በሰፊው እዩኝ ይላል። ከእይታ ተገልሎ በብቸኝነት መኖርን አክርሮ የተመለከተው ነው። በመጨረሻም ሆነ በሂደቱ ለብቻ ሲኖሩ ስደተኞቹም ሆነ ሠፋ ታይተዋል። ግን፣ ማንም ያንን በጤናው አይፈልገውም። እንደ ከኑሮ-መክበድ መዉጫ አድርጎ በመጨረሻ በዘጋው የመሪ ገፀባህሪዎቹ የጨዋታ-ባህል ትርክት ግን ከፍተኛ ቧልትአዊ ፌዝ እሚከውንበት ስኩ የአፍሪቃ መንግስትዎች ትችት አለ።
በስደተኞች እና ድሀ አፍሪቃአዊያን ችግሮች፣ ተጠያቂ እሚያደርገው አምባገነን ሀገር መሪዎችን ነው። ያን ጭብጥ ባቀረበበት ጥምቆራጭ ቧልታይአዊ (ኮሚካል) ፌዝ ማቅረቡ አንድ ልዩ-ዉቡ ነገሩ ነው።
ፍሬው በግንዱ ይንጠለጠላል። የልጅ ወደፊት፣ በብዛት በቤተሠቦቹ እና ወዲያው በከበበው ከባቢው ይጠረባል። ያ ማህበረሰብ ነው። እና ያ ወሳኝ ገሀድ፣ በይፋ እና ቅፅአዊ ስነሥርአት፣ ከጥንትአዊ አፍሪቃ ዘመን ጀምሮ፣ በመንግስት ተጠፍሮ እሚሾፈር ነው። በዛሬው ዘመን፣ የእዚህ አካል ዐብይ አንድ መገለጫው ወደቡ ስደተኛ እና ባይተዋር ልጆች እንዲንከራተቱ ማፍራት ከሆነ፣ አግልሎ-አግሎ መተቸቱ ጣዕም አለው። ለዉጡን መጥሪያው ነው።
የሰውልጅ ሲያድግ እሚኖረውን ኑሮ – የህይወት ወደፊቱን – ቤተሰቡ እና ከባቢው ስርኣት፣ በአንድነት ጠርበው ስጦታ አድርገው ያስረክቡታል። የአሁን ቤተሰብ እና ማህበረሰብ፣ የዜጋ ሙሉ ጠቢውን (ሆል ፊውቸር) መቼት (ሥፔስታይም) ነው። የወደፊቱ ጎልማሳ ግለሰብ በጊዜጉዞ (ታይንትራቨል) ወደኋላ ተጉዞ በማህበረሰቡ ዛሬ እየተነካካ ያለው ነው። የ “ሳይ-ፋይ” ሳቢስሜት (ሰንሴሽን) የሆነው ጊዜጉዞ፣ ማህበረሰብ ነው። ክሪስቶፈር ኖላን ወይም ጀምስ ቦንድ ሲጨመቁ ዋና መልእክትአቸው ያ ነው። የዛሬ ቆንጆ ማህበረሰብነት፣ ትላንትወዲያ ተጠንስሦ ትላንት የተገነባ ዛሬም የእሚቀጥል ወይም እሚጠበቅ ነው። ዛሬ በነገ የተቀጠለ ነው። ያ ጉልበታም ሀሳብ ስለሆነ ተተኳሪ ነው።
የዜጋ ነገው፣ በጊዜጉዞ የዛሬው ማህበረሰቡ ከተደረገ ይህ ፍካሬ ዋጋው ዕንቁ ነው። በእዚህ መሰረት የልብወለዱ ሦስቱ ጓደኞች የትርክታቸው ሂደት የመንግስት ክሽፈትን እንደጎለጎለ ነው። ሌላ እዉነት ማበጀት አይችልም። የለም። ሲያበቃ ግን፣ ኑሯቸው ሲከሽፍ ራሳቸውን ለማንቆለጳጰሥ የዘየዱት አድርጎ ለመዉሰድ ይመርጣል። በሌላ ቋንቋ፣ አያያዝአቸው እንጂ ፌዝአዊ ገሀዱ ግን ግንባርሥጋ ሀቅ ሆኖ እሚቀጥል ነው።
ሌላው ተያያዥ ነጥብ የዲሞክራሲ ጉዳዩ ነው። ከተሞከሩት በተሻለው በእዚህ ስርዓት ጉድለቶች በእርግጠኝነት አሉ። በዋናነት፣ የስነምጣኔ ዉስብስብነት ዛሬ መኖሩ ለስርአቱ ጓደኛ ከመሆን እና ኑሮን ከማበልፀግ ይልቅ፣ እሚገዳደረው ሀቅ ሆኗል። በተወሳሠበ እና ግዙፍ ስነምጣኔ ያሉ ድሀዎች በዲሞክራሲም ተከበው የተተዉ ናቸው። ዛሬም ያ ጥርጥር የሌለው ነው። ከቤተሰቦች አንዳንዶቹ ሲቆዩ ሌሎች መጉደላቸውን ጥርጥርየለሹ ልብወለዱ ያሰመረበት አንዱ የስርአቱ ቀዳዳው ነው። አሜሪካንን ኢፍፁምአዊ አድርጎ እንደገሀዱ በማምረር ከእዚህ ረገድ ፈንትዎት እንደሳለው ብዙ ሀያሲዎችም መስክረውለታል።
አሜሪካ ማስተካከል ያለባትን በልብወለዱ ዋና ይዘት በሂደቱ ሁሉ እንደሰበከው በአፍሪቃም ገሀዱ ግልጥ ነው። ብቻ እጅግ ሰፊ እና ስምጥ ነው። ማህበረሰብአዊ እና መንግስትአዊ ኃላፊነቶች በዝተው-ጠንክረው፣ እንዲሁም ስነምጣኔአዊ ገደብየለሽ ነፃነትዎች እንዲሁ ተቀንሠው፣ ብዙ ያሉብንን ጉድለትዎች ማስተካከል አለብን። የተሻለ ዕድል ለሁሉም ማድረሱን መንግስት እና ማህበረሰብ ማጠንከር ካልቻሉ፣ አቅም ያላቸው፣ በዲሞክራሲ ሲበለፅጉ፣ የሌላቸው የመፈንገል ዴሞክራሲአዊ እጣ ብቻ ይኖራቸዋል። ስለእዚህ፣ ይህኛው የክርክርቴ (አርጊመንት) ትልሙ፣ እጅግ ዉብ ነው። እጅግ ተገቢ ነው። ዳሩ አንድ ጥያቄም አለ። የቱም ዲሚክራሲ ግን በአፍሪቃ ገና የሌለ ነው። ምስኪን አፍሪቃ!

ሲጠቀለል፣ ችግሩ ማህበረሰብአዊ ነው። ምክንያቱም ዋና መድሀኒቱም ያው ማህበረሰብአዊ ነው እና። ማህበረሠብአዊ ሀላፊነቶች እና ስነስርአቶች ይህን ከአማካኝ በታች የተሳካለት ወይም እንዳተኮረበት ጭራሽ ያልተሳካለት ባይተዋር ሆኖ የመኖር ዉሳኔን እሚያሰማምር ዜጋ የማምረት ችግርአችንን እሚገፈትሩ ናቸው ተብሎ ይታሰባል። ይህን ጉዳይ አጨፍግጎ አይቶት ግን በአንድ ግለሰብ ሰፊ ሀላፊነቱን በመጨረሻ ጥሎታል። ያ ኃላፊነት መተኮር አለበት። ቢያንስ እዚህ። ምክንያቱም፣ እንዲያ ካልሆነከ፣ በአለው የአሁን ስርአቱ ላልወደቁት መዝናኛነት አድርጎ የፃፈው ካሎነ በቀረ ያ ኢምሉእአዊ መንፈሱ አለ። ለወደቀ ዜጋ፣ አንተው ወደቅህ ተመቻችተህ ኑር በቃ፣ ቢባል ዞሮ ማንም ደሴት ስላልሆነ፣ ማህበረሰብ እና ከባቢ እንደጠረበው ሆኖ ባይተዋርነቱን የሆነ ሰዓት ሊመረምር ይገደዳል። የበለጠ ማስመር እና ከዉይይቱ መጠቀም ያለብን ነን። ከቻለው ምክር ዝናብ፣ የልጅነት እና አስተዳደግ ክፍተቱን አሳሽ ካፊያ እሚሸሻለው ነው። ብቻውን ማንም ደሴት አይደለም። አዋቂዎች እና ማህበረሰብ መሪዎች፣ መንግስት ስርአቶች ነበሩ። ለምን አላበቁኝም? ያንን እማይጠይቅ የለም። ፍፁም ተገቢ ጥያቄ። የነገውም መልስ እና ጥያቄ የሆነ ነው። እንዳለው ታሪክ እሚረሳ ስለሆነ፣ ያም በማህበረሰብ ወደፊት መሪዎች ቸልታ ስለእሚከወን፣ የወደቀውን መጠየቅ፣ ጥቂት የኋሊት መመለስ ይሆናል።
የ ግራሀም Seven እምትለው ስኩ ሙዚቃ ያኔ ብትወጣ ኖሮ፣ የ ሜሪ ኦር ስሌቨሪ ኢን አሜሪካ ልብወለድ ልኮቱን (ሪፈረንስ) አቅልሎ ያለዘብለት ይሆን ነበር። ምክንያቱም ለመረዳት ያልከበደ ያለ ሀቅ አለ። ሰዎች በዘመነ፣ ወይም ኃላፊነትን ከምር ወስደው በእሚገኙበት፣ ዓለም ቢኖሩ፣ እሚቀነሱ መዓት ችግሮች አሉ። ቀድሞ ኃላፊነትን በእሚወስድ ትጉህ ማህበረሰብአዊ ቅንብር ዉስጥ፣ ለግለሰቦች ሁሉ በተሳካ የዜግነት መስመር የማደጊያቸው ነገር ከፍተኛ ቀና ዕድል ይሰጠዋል። ችግሮች ከታሪክ እንደተረሡት፣ ቢታወሡ፣ ይወገዳሉ። ወይም እንደእነ ሠፋ እጅግ አስጨናቂ ዐዉድ ላይ አይቀሩም።
እንዳተኮረበት፣ ከታሪክ ስህተት ተምረን ብቻ ሰዎችን በመቅረፅ እምናሳድግ እና ከባይተዋርነቱም ከኢስኬታማነቱም አዳኝ መሆን እንችላለን። እንዲህ ያሉ ስርአቶች በአፍሪቃ እና አዲስአበባ የሉም። እንኳን በስብእና በቅለው ሊያድጉ አለጥርጥር የተመዘገቡ ዜጋዎች እሚሆኑበት የአስተዳደርዎች ዕድልዎች በምንምአይሌ (ፌየር) መጠን የሉም። በአጭሩ፣ የልብወለዱ አስከፊ የአፍሪቃ ገፅታ አሳሣልን አይነት፣ በተመሣሳይ ተጋርተው እንደ ሰር ፖል ኮሊየር ያሉ የዳግ-ምርምር ዉጤቶች አስዉበው-አስከፍተው ያቀርቡታል። ስለእዚህ፣ ብዙዎች ወደታችኛው የኑሮ ደረጃ ቢዘቅጡ አዲስ አይደለም። ስደቱ ከዕውቅ ክፉ ምንጭ ነው። እራስክን ቻል ብሎ መምከሩ፣ አንዳንዴ ብቸኛው መዳኛ መንገድ ቢመስልም፣ እያንዳንዱ ግለሰብ ታሪክ ዘግቦ በልጅነት ተምሮ አቅም በራሱ አፅድቆ ለታላቅነት እሚፈጠር አይደለም። የትርክቱ ጉድለት ባይሰኝም፣ ይህ ትኩረት በማያወላዳ ቋንቋ፣ መቀጠሉ አንዱ መፍትሄ-ጎዳናው ነው። ሌላ አጓጓዞች፣ ቅንጦት፣ ወይም ዝብ-አረዳድ ናቸው። እንደተባለው፣ እንደአህጉር ክፉክፉ ወይም ስፖርት-ስፖርቱን ብቻ ተምረን ነው ያለንው። ዳሩ፣ ማህበረሠብ ማደግ ያለበት በጋራ የእያንዳንዱን አባል ዜጋ ችግሮች ተጋርቶ በቀላሉ በመፍታት ነው። ሁሉም ዜጋ ወል ሆኖ ለእያንዳንዱ ዜጋ መድረስ ይችላል። ያን ስርአት ማቋቋም ይቻለዋል። ያኔ አንዱ ግለሰብ ለራሱ አይከሽፍም። ቢያንስ በከፋ ደረጃ። ያንን ስርአት ግን መገንባቱ በአፍሪቃ የለም። ከልብወለዱ ዘመን የበለጠ ብዙዎች ከአህጉረአፍሪቃ በእሚፈልሱበት ወቅት አብዮቱን ናፍቆ በእዛው መቅረት አላባራም።
ልጆችን ገና በእድሜ ማለዳ ማነፅ ሢቻል፣ አጓጉል ማህበረሠብአዊ ኑባሬ እና አያያዝ፣ በቀዝቃዛ ስንፍና አሳድጓቸው፣ የጎልማሳ ዕዳ እንዲሆኑ እያደረገብን ነው። ከዜጋአዊያን (ሲቪሊያን) በተለየ ደግሞ ተጠቂ ዜጋዎች የበለጠ ገፈት ወሳጅ ተደርገው ይገኛሉ። ዶይስቶቨስኪ እንዳለው፣ በተገለሉት ዜጎች ሁኔታ ማህበረሰብ እንደእሚለካ፣ አሁንም የበለጠ የቤትስራ።
ንጥል ግለሰብ ሀላፊነት መሸከም አለበት። ግን በቂ ዝግጅት እና ትኩረት ማህበረሰብ ቀድሞ ሊሸከም እና ሊያሸክመው ይገባ አለ። ግለሰቡን በሀላፊነት መም ሊያመጣው ያኔ ይችላል። ከመውደቅ እሚዳነው በገራ ስርአትአማ ጉዞው ሲከወን ነው።
ልብወለዱን ይህን ስንጠይቅ መፈተሽ ሞክሯል። ደህና መልስም አለው። አቂያቂይ ፌዝ እና ምስጥ ንፅጽርአዊ ገጽታዎቹ ሁሉን ባይጠቀልሉም ኧውአስብል (አዌ ኢንስፓየሪንግ) ናቸው። ማህበረሰብን እና መንግስትን ደህና አድርጎ ተችቶልናል። ወድቀናል። ከታሪክም አልተማርንም ብሎ ሰድቦናል። ዳሩ፣ ይህ ከየቱም ግለሰብአዊ ዉድቀትነት ይልቅ፣ የወል ዝርክርክነትአችን ነው። እሚንገዳገድ ኢትርፍአማ ሱቅ ካለን – ወይም በእየመንገድ ዳርቻው ካለን – ከየተደበቅንበት እነሆ አብረን መጥተን አብረን እንደወደቅን ነን። እስከቀጣይ ሳቢስሜትአዊ (ሰንሴሽናል) ልብወለድ፨


ጉርሻነት (ትራይቪያ)
ሠፋ ወደገበያ ለገና ስጦታ ሊገዛ ወጥቶ ቀድሞ ለቤተሰቦቹ እሚሆን ያሳሥል። በኋላ ለጁዲት አንድ ነገር ለመግዛት በማሠብ ይጠመዳል። መፅሐፍ ሊገዛላት ወሰነ። የዲኪንሰንን ስብስብ ግጥሞች ገዛ። ትርክቶ ቆይቶ፣ ስጦታዎቹን ለሁሉም ያደርሳል። በኋላ ግን ካላስተዋልን ያመልጠናል። ለጁዲት የታሰበውን ያንን መፅሐፉን ለእናቱ እሚሰጣት ሥጦታ ሆኖ እምናገኘውን ነው፨

የግርጌ ማስታወሻ፤


ጥሬገንዘብ በወረቀት መገበያያ ገንዘብ የተገለጠን ንብረት ብቻ ሲጠቁም መዳፍገንዘብ ግን በእጅ እሚጨበጥ አሁን እና እዛው ያለ ጥሬ ገንዘቡን ይገልጣል። የቀደመው የወረቀት ብር ወይም ኖት እንደማለትም ነው። ተከታዩ፣ ያንን በገሀድ ስለመጨበጥ ነው።

የእዚህ ፅሑፍ አዘጋጅ የልብወለዱ ግምገማ ንባብ እሚቻል ነው። Binyam Hailemeskel, Dv Lottery: The Alchamy to Eternal Foundation, ተአዶ. (PDF = ተንቀሳቃሽ አሀዝአዊ ዶሴ) ያግኙ። ወይም http://www.archives.org ያስሡት፨

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s