Categories
My Outlet (የግል ኬላ)

ምእራፍ-፯

መስፍን ጎንለጎን ምእራፍ ፯፨

፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
፯ የጎንለጎን ፍሬ

ምእራፍ ሰባትን በ ተአዶ. (PDF).

አርብ ጠዋት ናሆም ወደ ቀጠሮው ለመድረስ በጊዜ ተነስቶ ተሰናዳ። መስን ጥቂት ድንጋይዎቹን ቀጥሎ በመልቀም አግዞ ወደ ሁዳድ አራት ሰፈር፣ ፊት ታጥቦ ጥርስ ቦርሾ ቁርስ ሳያደርግ ተጓዘ። ፀጥ ባለ የማለዳ ድባብ እየተማረከ በእርሻው መጀመሪአ ተግባርአዊ ትዉዉቅ ሳይጨነቅ ወደ መንደሩ ደረሰ፨
ጋሽ ተሻገር ጋቢአቸውን አዘንጥፈው በሬዎች ጀርባ ቁሳቁስ ሲአሰናዱ ደረሰ። በፍጥነት ወደ እርፉ ተመለከተ። እንደ ገመተው አለቅጥ የረዘመ እርፍ ነበር። “አጠር ያለ እርፍ የለዎትም?” እንደ ተካነ ለመምሰል እየጣረ ያጠናውን አስቦ ብቻ ጠየቀ። ሰላምታ ተለዋውጠው በኪራይ ያገኙአቸውን ከብትዎች እየነዱ ወደ መሬቱ ተሻገሩ። በእርፉ መርዘም የአካል ፈተና ስለነበር ጥቂት ሃሳብ ገብቶት እንደ እሚሆን ሁሉን ለመያዝ በፍፁም ሃሳብ ወሰነ። ሰርቆ አይቶአቸው በተፈጠረው ኩነት ተደምሞ በግሉ ሳቅ ይል አለ። ስለመሬትአቸው ረዥም ታሪክ አጫውተውት በቅርብ ከተማ መግባት እና መጦር ስለ አቀዱ እንደ ቀናነሱት፣ ምን አልባት የመጨረሻ እርሻአቸው እንደ ሆነ እዳሪው ላይ ደርሰው አስረዱት። ለመሳተፍ ስለ እሚጓጉ እና ፍቅርአቸው ለግብርናው ትልቅ ስለ ነበር ባገኘው ተቆጣጣሪ እና አጋዥ ፊት የመሞከር ዕድል ይበልጥ ተበረታትቶ በሬዎቹን ጠመዱ። ቀንበሩን አመቻችተው ወደ መሬቷ ሰክተው ጋሽ ተሻገር ዛፍ ሥር አረፍ አሉ፨
መስ በሬዎቹን በመግረፍ ለማንቀሳቀስ ሲጥር ትልቅ የእርካታ ስሜት ቸፈፈበት። ቀድሞ ያልተሰማ ስሜት። መጀመሪአው በሬ ለእርሻ በማዘዝ የመግረፍ ድንቅ ስሜት። ወደ ልጅነት የመመለስ ትልቅ ስሜት። እርሱነቱ የተሟላ ያክል አንድአች አሟይ ኢመደበኛ ደስታ ከበበ ው። በሬዎቹ “አንተ ከተሜ!” ብለው እንቢ አላሉም። በታላቅ ታዛዥነት መራመድ ጀመሩ። ሞፈሩ ተገፋ። የመጀመሪአዋ አፈር ተፈንቅላ መልሳ ወደቀች። ናሆም በተጨማሪ እርካታ ጥርሱን ብልጭ አደረገ። አፈሩን በመመልከት ፈዘዘ። “እንዴ ምታው እንጂ ይኼ ዳለቻው እማ ትንሽ አንቀላፍቶ አለ መሰል!” ጋሽ ተሻገር ከሰረገበት ድንቅ ደስታ ባህር አወጡት። አፈሩ ድጋሚ ተፈነቀለ። ደስታውን እየዋጠ “ሂድ!” በማለት ጮኸ እና ጅራፉን ደገመ። ከብትዎቹ በጩኸት መራመዱን ፈጠን አድርገው ቀጠሉ። “እንዲኣ!” ጋሽ ተሻገር እርካታ ሲምጉ፤ ናሆም ታላቅ ደስታው እንዲዘልግ አተኩሮ ወደ ሥራው ሰመጠ። በከብትዎቹ አረማመድ መጠን መሄድ ስላቃተው እንዳይመለከቱት ቶሎ ብሎ ሮጥሮጥ በማለት የከብትዎቹን አረማመድ ተመቻቸ። በአፈጣጠኑ ተጠቅሞ በዛ ያትልም ፈነቃቅሎ ተጓዘ። ዞር ብሎ መመልከት እንደ እማይችል በማስተዋል ከመመልከት ማተኮር በእሚል ወደ ሥራ ው ብቻ ተመሰጠ። እንደ አብዛኛው ኢትዮጵያአዊ ከከብትዎቹ ቂጥ ሥር ኩስኩስ ማለቱን ቀጥሎ የአንዱ በሬ እበት እና ፈስ ተላከበት። ከፍተኛ ሳቅ ከበበው እና መልሶ ሥራ እንደ ያዘ በማሰብ ፈሱን ችሎ እበቱን ረገጥ አድርጎ አለፈ ው። ትልሙ ተቋጨ። ጋሽ ተሻገር ከእሩቅ “አዙረህው ና ይ!” በማለት ሲጮኹ ያረሰውን ትልም ተመልክቶ ድንቅ ስሜት ለነብሱ ቸረ። የመጀመሪአ ሥራው እንደ ሆነ አስቦ መደሰቱ የላቀ ሆነ። ‘ስኬትአማ አያያዝ!’ ከብትዎቹን እሮጦ ቀድሞ በማዞር እንደ ቀደመ ማረሻውን ተከለ። በተሻለ ፍጥነት ተመልሶ መጣ። ጋሽ ተሻገር “ደህና ነህ ምንም አትል!” በማለት አስተያየትአቸውን ሲቸሩት ተደስቶ ፈገግ አለ። በሦስተኛው መመለስ ጊዜ ትልሙን ሰፋ አድርጎ በፈለመጨነቅ እንዲመለስ አድርገውት ተቀመጡ። “የልምድ ነገር!” ለእራሱ በ ዝግታ ተናገረ። በተሰጠው ስፋት ሞፈሩን ቀብሮ ተጓዘ። ተመለሰ። መሬቱ ከማጠሩ የተነሳ በሁለት ሰዓት ተኩል ዉስጥ እዳሪው ወደ ማሣነት ተዘጋጅቶ ተቀመጠ፨
“ትንሽ አረፈድን መሰል ዬ። በቀረ ደህና ነህ ኧረ። ፈርቼ ነበር አጀማመርህን አይቼ። ግን ደህና ነህ! ዬ!” የ ጋሽ ተሻገር አስተያየትኤ ይህ ሲሆን በመጀመሪአ እርሻው ናሆም ከፍተኛ ኩራት ተሰምቶት መርካቱን ቀጠለ። ቁሳቁስዎቹን ቀንበሩን መፍታት አላቅቀው ናሆም ተሸከመ። ጋሽ ተሻገር ከብትዎቹን በመንዳት እየተጨዋወቱ ወደ ቤት አዘገሙ። ተጣጥቦ ቁርሱን ተጋብዞ ከወጣቱ መፃተኛ ያክል ብቸኛነት ከተሰማው ዘመድአቸው የተባለ ወጣት ጋር አብሮ እየተጨዋወቱ ቆዩ። ጋሽ ተሻገር ደስታአቸው ልቆ መሬትአቸው አለሥራ አለማረፍ ተደስተው ወደርየለሽ ስሜትአቸው ሰፍፎ በመደሰት ቆዩ እና ስለ ቀጣዩ ሁኔታ ጠየቁ። “ሰኞ ደግሞ ማልደህ ና! እንዘራው አለ!” “እሺ ጋሽ ተሻገር!” “ያው አንተ አንድ ሦስትኛዋን ትበላ አለህ ታዲኣ!” ናሆም ጉዳዩ ስለ ተነሳ ተደስቶ “እኔ እንኳ መሬት ዋ አሁኑኑ ቢሰጠኝ እደሰት ነበር ጋሼ!” አላቸው። ለአትክልትዎች እርሻ እንደ ተዘጋጀ ሲገልጥ ከ ጤፍ በቀር ቢታረስ ለአጨዳ ቢቀልል ለ ዉቅያ ግን ያነሰ መጠን መዉቃቱ እንደ እሚከብድ ገለፁ። ሃሳቡ ግን መሬቱን መዉሰድ እንደ ነበር ችክ ብሎ ሲአስረዳ ተስማሙ። “ይህን ያኽል አይከፋ ለነገሩ። ስለ አልተለመደ እንጂ ብዙም አይጎዳ ዉቂያውም ቢሆን። እንዳሻህ! አንተ ዝራበት ያሻህን!” ጋሽ ተሻገር፣ የጎረቤት ልጅአቸውን ከፍለው ከእምታበስለው መብል የባቄላ ንፍሮውን እየተመገቡ እንደ ተስማሙ ሲነግሩት ናሆም ተደስቶ ሊስምአቸው ቀረበ። ያታክልት ዘርዎች ለመሰብሰብ ምርጡን መንገድ ሲአቅድ “ሰኞ እንከፍለው አለ መሬትህን!” አሉት። ተስማምቶ ጨዋታው በቡና ቀጥሎ ምሣ ሰዓት ሲደርስ ወደ ሰፈሩ ለመመለስ ተለየ። ‘እማይረሳ ቀን!’

ሰኞ በ ተመሳሳይ ሁኔታ የ ጋሽ ተሻገርን ቤት በ ማለዳ ደርሶ አንኳኳ። እሚዘራውን አዘጋጅተው ወደ ሳሎን በለመደ ጋቢአቸው ተጀቡነው ሰላምታ ሰጡት። ተያይዘው በመዉረድ ከብትዎቹን በመከተል ዘሩ።
የግብርና ተቋሙ ወዲአው ለናሆም እሚሰጠው እንደ ሌለ ተረዳ። ዘሩ ካላቸው ገበሬዎች፣ መጠነኛ አሰሳ አድርጎ ለዘርዎቹ ፍለጋ ሙከራ አደረገ። አልተሳካም። ከዘር ሱቅ ያገኘውን፣ ለመሸመት ተገደደ። የቆስጣ፣ ካሮት፣ ቀይስር፣ ድንች፣ ቃሪአ፣ ነጭ ሽንኩርት፣ እና ዉሃ እማይቋጥር መሬት መሆኑን ከአረጋገጠ አንድ ትልሙን ቲማቲም ሊሞክርበት ዘርዎቹን ሸክፎ ሄደ። መሬቱን ቆርሰው ከሰጡት በኋላ እሚዘራውን አልጠየቁትም። ብቻ መሬቱ ዉሃ አይተኛበትም ብለው፣ ስለ እሚለዩት በመቆጨት ጭምር ሲአብራሩለት ዘርዎቹን ሁሉ በእየትልሙ ተከለ። እንዳይረገጡ አሳስቦ ከዘሩ በኋላ ወደ ቤት ተመለሱ። የተለመደ የቁርስ እና ቡና መስተንግዶ ተደርጎለት አመስግኖ በ ሳምንቱ እንደ እሚመለስ ቃል ገብቶ ተለየ፨

ሩት በ የ ፋሲካይት ኅዋአዊከተማ ምልልስ እየአደረገች ማጥናትዋን ቀጥላ ቆየች። አንድ እረፋድ እዛ ዉላ ወደ ቤት ስትመለስ ወደ ዓሊ ቤት ዝምብላ ሳታስበው አመራች። ዓሊ ብቻውን ስለ ነበር በመምጣቷ ተደንቆ አስገባት። የገጠማትን የተግባርአዊ ተሞክሮ አንስታ ሲጨዋወቱ ቆዩ። ጭር ሲል ስለ ሠሚራ ጠየቀች። ለለቅሶ እንደ ወጡ ነግሮ ሻይ መጠጣቱን ተያያዙ፨
በ ትመ. ብዙ መማረክ የእማያሳየው ዓሊ የመዝናኛ ጣቢአ ከፍቶላት ሲጨዋወቱ ቆዩ እና የጉዞው ጉዳይ ተነሳ። “እስቲ ስለ ባህል መዳኒት ትንሽ አዉራኝ እና አስተዋውቀኝ!” ጨዋታውን ከፈተ ች። ዓሊ በቀላል ስብእናው ነገሩን አቀለለ። ምንም ነገር ቢሆን አንዴ ከተረዳው በኋላ እንደ ተራ ወሬ አቅልሎ እሚአወራ ስለ ሆነ ከሩት የመዝናናት ፀባይ ጋር ይህ ነገረስራው ይገጣጠም ነበር። “ባህል መድሃኒትዎች፣ ከመንፈስአዊው እሚለዩ ናቸው። እንግዲህ ለጊዜው ያጠናሁት ለአንዳንድ ቁስል ወለምታ፣ አብሽ፣ አዙሪት፣ ወዘተ. እሚሰጡትን ብቻ ነው። ከቅጠል ብቻ እሚሰበሰብ አይደለም። ከብዙ የቤት እቃዎች እና ተፈጥሮአዊ ነገርዎች ይዘጋጅ አለ።”
ሩት መጠነኛ መግቢአ እንደ ተሰጣት አምና ምሳሌ ጠየቀች። “ለ ምሳሌ፣…ብርድ በሞቀ ዉሃ፣ ተልባ ተደርጎ የተመታው አካልሽ ላይ በነጭ ጨርቅ ይጠቀለልበት አለ። ተጠቅልለሽ መተኛት ነው። ስትነቂ ብዙ ጊዜ የለም!” “ያለ ህክምና እና መርፌ?!” ሩት ተደምማ ጠየቀች። “አዎን! ለ ምሳሌ ግድግዳ ተደግፎ ጉልበቴ መተጣጠፍ አቅቶት ብርድ መትቶት ያቅ አለ።” ፈገግ ብሎ በሶፋው ላይ ፈልሰስ አለ። “ግን በእዛ መስተንግዶ አንድ ሌሊት ጀርባ ወልቆ ሄደ።” ሩት ተደምማ በተገማሪ የባህል መድሃኒትዎች እና ህክምና ማብራሪአ ስትቀበል ቆይታ ጨዋታው ሞቀ። ሳታስበው በሣቁ መሃል ወደ ጎኗ አዘንብላ ዓሊን ከንፈር ላይ ከንፈሩዋን አገኘች። ለአፍታ እንደ ሳመችው ዓሊም እንደ ተመሰጠ ቆየ፨
ድንገት ከመቅጽበት የተከሰተውን ኩነት መነሻውን ለማሰብ ሩት ሞከረች። የመነሻ ቅጽበት እና ሃሳቡ አልታወስ አላት። መሳሙ ጋብ ብሎ መተፋፈር ሆነ። ዓሊም ሰክኖ አስተዋለ። ሩት ትጀምረው አትጀምረው ማወቅ ሁሉ ተሳናት። ነገሩ እንዲቀልል ብላ “ቅጠል አስነካህኝ እንዴ?” ፍራቻ እንደ ያዛት አፍዋን እየጠረገች ጠየቀች። ዓሊ መረጋጋቱን አተኮረበት። ጥቂት አዉጠንጥኖ “ይገጥም አለ!” ብቻ በማለት አለፈው። ከልብ ባይሆንም በ ትመ.ው አፍጥጠው እንደ ቆዩ፣ ሩት ዓሊን አመስግና መልሳም ለሁኔታው ይቅርታ ጠየቀች። የጀመረችው እንደ ሆነች እንዲሁ ከቅጽበትአዊነቱ የተነሳ ባታስታውሰውም አመነች። እንደ ተሳሳቢ (ማግኔት) የተፈጠረ ቅጽበት ሳይታደን እና ሳያድግ መመለሱ ትክክለኛነት እንደ አለው ተሰማት። በድጋሚ ለሁሉም መስተንግዶ አመስግና ወደ ቤቷ እንዲሸኛት አደረገች። ከበሩ ጥቂት ራቅ አድርጎ ባዶ ቤቱን እያሰበ “በይ ሂጂ! እማይገጥም ስለሌለ የተከሰተ ነገር የለም እመኚው እና እለፊው እንግዲህ!” “ዕፀ መሰውር እስክታገኝ በርታልን በቃ!” ጨዋታውን ለመቀየር አስተያየት አቅርባ ጥቂት ተጨዋውተው ለመሄድ ዓሊን ወደ ቤቱ መለሰች፨
ተሰናብታ በጉዳዩ እየተብሰለሰለች “ያልተፈጠረ ያክል” እሚለው አስደስቷት የቤቷን መስመር ተያያዘች፨

በ ሦስትኛው ቀን ለፍኖት ማህበረንባብ ሁሉም ሲሰባሰብ የነ ሩት ጉዳይ ሙሉኛ ተረስቶ ነበር። ዓሊም በአዲስ ጨዋታ ነገሩ ከቶ መሸሹን በስውር አሳውቆ ማህበሩ በተለመደው የዕሁድ ስምንት ሰዓት በየ ሃያአንድ ቀኑ እሚያዝ ዝግጅት ሊጀመር ሆነ። አስሩም አባልዎች በሰዓቱ ተሰብስበው የእለቱን አጀንዳ ናሆም አቀረበ። ባለፈው ማህበር የ ቀረበ የ ቡድኑ አባልዎች ሁሉ አስተያየትኤዎች በናሆም ተተይቦ ለይፋ አገልግሎት ወደ አንድ ወጥ ጽሑፍነት ተቀይሮ ተነበበ። በአምስት ገጽዎች የመጽሐፉ ትርክት፣ ጭብጥ፣ አንድመስመሬ (በ አንድ መስመር የ ትልም ሃሳቡን መጭመቅ)፣ አስር እማይበልጡ ጥቅስዎች፣ እና አስተያየትኤዎች ተነበቡ። በቀላል ድምጽ ብልጫ በአሃዝአዊ ጦማር አድራሻአቸው እና ትዊተር ገጽአቸው ሊለጠፍ ተፈቀደ፨

በ ማለዳ ተስነው ጥርስ እና ፊት ፀድቶ፣ የተለመደ እሩጫ እና እንቅስቃሴ ብሩን አስከትለው ካሳለፉ በኋላ ናሆም በብሩ አካል መዘጋጀት ተደምሞ አበረታታው። በበለጠ ፍጥነት እና በአነሰ መቆራረጥ በመሮጥ የተለመደ ሥፍራው ላይ ሲደርስ ተመለሰ። “ቀጣይ መስ ብዙ ንደ አልራቀ ዛሬ፣ አብረንው ደግሞ እንሮጥ አለ!” ተስፋውን ሰጥቶ ብዙ ወደ አልራቀ መስ እንዲሄድ ወንድሙን ነገረ። ናሆም ወደ መስ ብሩን ፈገግ ብሎ በመመልከት ተለይቶ ሮጠ፨
ወደ ቤት ሲመለሱ፣ የቤታቸውን ግድግዳ ለ ማሳደግ ከ ወለሉ ጀምሮ የ ደረሰ ጭቃአቸውን ተጠቅመው ግንብ መደርደሩን ተያያዙት። ቀኑን ሙሉ በመገንባት፣ ብሩ እና ናሆም በ ማገዝ ወፍራሙ ግድግዳ ከ አንድሜትር በላይ ሰገገ። መስ እረፍቱን ጥቂት በማረፍ ለ ማሳለፍ “ጊዜ የሌለው መቸኮል አለበት” በ እሚል መርህ ነገሩን ወደ ፍፃሜ ቶሎ ለማድረስ ታተረ። ሥራ በ ማሻገር ነገን ተስፋ ከ ማድረግ አሁንን በ መበርታት ነገን ማረፍ እሚል መርኅ ስለነበረው በፈጠነ አካሄድ ወደ ሥራው ወደብ እንዲደርሱ መጠመዱን አምኖ ተነሳ። የ ተጀመረ ነገር በ እርግጥም መዘናጋት እንዳያዘገየው ይህ አሳቡ ይደግፈው ነበር። ተቆጣረከ ሥራን ቶሎ ጨርሶ መቀመጥ ስለ ማረፉን እሚከጅል፣ በ እሚሰራው ሁሉ ማብቂአ ጊዜን የ ቀደመ አፈፃፀም ይከውን ነበር፨
በ ማግስቱም ሥራውን ቀጥለው ግድግዳው የበር ቁመት ሙሉ ያዘ። በንድፉ መሰረት የፊትለፊት ግድግዳው ላይ መስታወት እንዲገጠም ከበሩ በላይ ክፍት ሲተው፣ የሁለቱን ክፍልዎች እሚለየው ግድግዳም ገና ከአንድ ተኩል ሜትር ላይ ቆመ። የቀሩት ግድግዳዎች እስከ ጣሪአ ዘልገው ገጠሙ። የመስ መጨረሻ ወጪ መስታወት የፊት ግድግዳው ጫፍ ከጣሪአው ወደ በሩ ቁመት ድረስ ገጥሞ፣ በር እና መስኮትዎችን ማበጀት እና መብራትዎች መዘርጋቱ ሆነ፨
ሲሰሩ ዉለው፣ ብሩ እና ዮስ ወደ ዮስ ቤት ለእረፍት ወጡ። መስታወት አዝዘው ለነገ ጠዋት መግጠሙ ወደ ቀጠሮ ስፍራው ናሆም እና መስ አረው ወጡ። እሚ እንደ ለመደችው ከቢግ ጋር ወደ ኩሽና ገብታ እራት ማሰናዳቱን ጀመረ ች። የቢግ ሙያን በማድነቅ ሽንኩርት ከትፎ ሲአቀብላት ከፍተኛ እሪታ እና ጩኸት ተደመጠ። በየት እግር ወይም ክንፍ እንደ ሄደች እሚ አታውቅም። እንደ ንፋስ በመብረር ወደ ጊቢው ሮጠች። ባቤ እና ጢዩ በመሰላሉ ተሰቅለው ወደ ከቤቱ በር አናት ላይ ክፍት ቦታውን ሲጎበኙ ባቤ ወደ ዉጭ ወድቆ ነበር። ባቤ ግራ እግሩን በደመነብስ ይዞ ከመጮኽ ወደ ማቃሰት ተመለሰ። ከፍተኛ ጉዳት የ አስተናገደ ሆኖ እራሱን ሳተ። ጢዩ በማልቀስ ስትፈዝዝ እሚ የተቀሰቀሰች ጮለቅ ጩኸትም ተሰምቷት ጢዩን ወደ ልጅቷ በጩኸት ላከች። ቢግ እሚን ተከትሎ የባቤን ሰውነት እሚ ተከትላ ወደ ቤተሐኪም ለመጓዝ ተሯሯጡ። የሦስትእግር ተሽከርካሪውን ከረዘመ እግር ጉዞ እና እሩጫ በኋላ ቀጥረው ወደ ከተማው ብቸኛ ጤና ማዕከል እንዲወስድ አዘዙት፨
እሚ በመጨነቅ እንባ ማፍሰስ እና ክዉታ የልጇን ሰውነት ብትፈትሽም ባቤ ዓይንዎቹ በመስመጥ እራሱን እማያውቅ ሆነ። “ወይኔ ምን ሆንክብኝ እንደው!” እሚ ማልቀስዋን ስታበዛ ወጣቱ አሽከርካሪ እየአፅናናት በተቻለ ፍጥነት እና አቆራራጭ መንገድዎች ታግዞ፣ ከከተማው ወጣ ወደ አለው ፋሲካይት ጤና ማዕከል አደረሳት። “ኅዋአዊከተማው ጤናጣቢፈ ሰሞኑን ከፍቶ ነበር። ግን አካሚ አንድ ሰው እንኳ የለውም። እዚህ ይሻል አለ በርቱ እንግዲህ!” ልጁን ሲአወርዱ ለእነ እሚ አሳወቀ። እሚ በደመነብስ ሆና በእርጋታ ወጥታ መሮጥ ስትያያዝ ሹፌሩ ጮኸ። “ሂሳብ! ሂሳብ!” እሚ ምንም ቦርሳ አልያዘችም። ቢግ በኪሱ ሃያ ብርዎች ቆይተው ነበር። አዉጥቶ አስረከበ። ብዙ ቢጠብቅም ሁኔታውን ተረድቶ “ይቅናአቹህ!” ብሎ ሲመለስ እሚ በከፊል ልቧ መጨነቅ ይዟት ስለ ነበር ተመልሳ መሯሯጡን ጀመረች። ወደ ዉስጥ ሲገቡ ድንገትኛ ክፍሉ በአንዲት ነርስ አስተናጋጅነት ተቀበለአቸው። “እባክሽ ልጄን! ልጄን!” እሚ ልጁን አስረክባ በመሬቱ ላይ ተንበረከከች እና ጮኸች። ነርሷ እንዲረጋጉ ተናግራ “ምን ገጥሞት ነው?” በመዋከብ ጠየቀች። “ከግድግዳ ወድቆ!” “ቢቢግ ሲመልስ እሚ ማልቀሷ ቀጠለ። “ደንግጦ ነው እሚሆነው…” ቀለል ያሉ ልብ ምት እና ትትፋሽ ተሻዎች ከውና ተናገረ ች። “ደህና ነው?” እሚ እራስዋን በመርሳት አፋፋፍ ሆና ጠየቀ ች። ጥቂት ረጋ ለማለት እሚረዳ መረጃ መሰላት። ነርሷ እግሩን እንደ ተጎዳ አስተውላ መረጃዎች በመጠየቅ ቆይታ ወደ ሃኪም እይታ ይዛው ሄደች። እነ እሚ እንዲቆዩ ተናግራ ወጣች። ቀላል እንደ እሚመስል በማሳወቅ ግን ገና ምርመራ እንዲደረግ እንደ ሆነ አሳስባ ቢግ እሚን እንዲአረጋጋ መክራ ሄደች፨
የ ተመለከተው ሃኪም የባቤ ግራ እግር እንደ ታጠፈ እና በግራ ክንዱም መሰል ጉዳት እንደ ደረሰ፣ አስተዋለ። ጥቂት አናቱ ከተመታ በማለት ስጋት ይዞት ሲጠረጥር እና ሲመረምር ቆየ። እንዲአርፍ ወስኖ እነ እሚን ማነጋገር ጀመረ። “ይነቃ አለ አሁን ብለን እንገምት አለን!” እሚ ይህ ሲነገራት ልቧ በአጣብቂኝ ሠቀቀን ተወግቶ ተያዘባት። በ መቁነጥነጥ እና እራስ መርገም፣ ዳግምአዊ ግመታ (ሰከንድ ገሲንግ) መብከንከን ጀመረች። ሃኪሙ ዉሃ አምጥቶ እንድትጠጣ እና እንድትረጋጋ፣ ከክዉታ እንድትመለስ እረድቶ አብሮአቸው በመጠበቂአ ወንበር ተቀመጠ። እየተጨዋወቱ ሳለ እነ መስ ድንገት ደረሱ፨
ገና ስታየው “መስ…!” ብቻ ብላ እሚ ሌላ ሳትጨምረደ የመስን እጅዎች አፈፍ አድርጋ ይዛ አለቀሰች። መስ እና ናሆም ቤት ሲገቡ ዜናውን ከጢዩ ሰምተው ሌላ ስፍራ ስለሌለ ወደ እዚህ ማዕከል ተንደረደሩ። የእሚ ቃል ለወቀሳ ይሁን ከጭንቀት የመጣ ባለማወቅ ሆኖ ብቻ ስለ ሁኔታው ለማወቅ ከሃሳቡ ተመለሰ። “ደህና… ነው አሁን!?” በፍራቻ ከታመቀ ትንፉሽ ጋር እየታገለ ተናገረ። ሃኪሙ ተነስቶ ማን እንደ ሆኑ በመጠየቅ አቋረጠ። ቤተሰብ እንደ ሆኑ ሲረዳ ደህና እንደ እሚሆን ግምቱን ሰጠ።
“ከ ታመመ ወደ አዲስአበባ እንዲላክ እናመቻች አለን። ይንቃ እና ሁኔታውን እንመልከት!” ሃኪሙ በመስከን ሲናገር ተፅናኑ። የአካሚ አብሮት እና መገንዘብ ትልቅ እፎይታ እሚቸር ነው ብሎ መስ ማስተዋል አደረገ። ስለ መሰላሉ በነበረበት መተው ሲናደድ እና መስ እራሱን ሲረግም፣ እሚ ከ ተፅናኝነቱ ወደ ማፅናናቱ ዞረች። ሃኪሙ ጨዋታውን ለማርገብ ዘና ባለ አቀራረብ ስለጥንቃቄ በመምከር እና በማውራት እየተጨዋወቱ ሳለ፣ ባቤ አጠገቡ ሆና ስትፈትሽ የቆየች ነርስ ተጣራች። ባቤ እንደ ነቃ ሁሉም ዘው በማለት የተኛበትን ከበቡ። እሪታውን ሲአቀልጥ ከድንጋጤ እንደ ሆነ ሃኪሙ ተገንዝቦ ለማረጋጋት ሞከረ። ቤተሰቡን እንዲአይ አድርጎ ዉጭ እንዲወጡ አደረገ። ከነርሷ ጋር ደንደን ያለ ሰውነት ያለው ባለ ነጭ ጋዋኑ ሃኪም መነፅር እየአስተካከለ ስለ ገጠመው ከአስታወሰ ባቤን ጠየቀ። ቢግን በአዉቆታ ጠይቆ እንደ አወቀው “ታላቁ ሰዓሊ ሃብታሙ በረከት ወይም ባቤ! እንደ ሜትር አፈወርቅ ተክሌ ልትሆን ነዋ!” ባቤ እራሱን በአዎንታ ነቀነቀ። “እና ምን እየፈመመህ ነው?” በፍራቻ ተዉጦ መዉደቁን እና ግራ እግር እና እጁ እንደ ታመሙ አሳወቀ። ሃኪሙ ወለምታ እንደ ሆነ አረጋግጦ “ትድን አለህ! አይዞህ! የሰዓሊ ሰውነት እንዲበላሽ አናደርግም! በተለይ ደግሞ እግር እና እጅ!” ፈገግ አለለት። ባቤ ከፍተኛ ያልተገነዘበው እርካታ በቀረበለት እንክብካቤ አልፎ ተሰማው። “ሌላ የአመመህስ?” “ምንም!”
ሃኪሙ በማረጋጋት ብዙ እንደ እሚሻለው አስቦ አረጋግቶ በጫወታ መሳሳቅ ጀመሩ። እጁ ያነሰ ጉዳት ስለ ነበር በመታሸት እንዲድን ሙያአዊ አስተያየቱን ሰጠ። እግሩ ግን በጨረር እንዲመረመር አዘዘ፨
ብዙም ታካሚ በሌለበት ስለ ደረሱ ጨረር የተመለከተው እግሩ ጥቂት ስብራት አስመለከተ ች። በተገቢ ህክምና ፈጽሞ እንደ እሚስተካከል ሃኪሙ አረጋግጦ በማረጋጋት በመታሸግ እንዲታከም አደረገ። ተባባሪ እና እንደ ቤተሰብ እሚቀርበው ሃኪም ጤናአዊ መስተንግዶውን አድረወጎለት ከምሽቱ አራት ሰዓት ሲል ወደ ቤት ለመመለስ ሃኪምአቸውን እጅነስተው አመሰገኑ። ባቤ በመስ እቅፋት ሆኖ ሃኪሙን እንዲአመሰግን ሲታዘዝ “አድገህ አንድ ትልቅ ሰዓሊ ሁን እና ክፈለኝ!” ሃኪሙ ፈገግታን ቸሮ በታካሚው ሁኔታ ተነክቶ መለሰለት። እንዲጠነቀቅ አስጠንቅቆ ለክትትል ቀጠሮ ሰጥቶ ሸኘአቸው፨
ብሩ በመስ ትእዛዝ ወደ ቤት ተመልሶ ጮለቅን እና ጢዩን ሲንከባከብ አምሽቶ የተኙ እህትዎቹ ትተውት ለብቻው ተቀበለአቸው። ባቤ ብዙ ህመም ሳይሰማው፣ መገሰፁም እስኪድን ተዘልሎለት በጨወታ ህመሙን እረስቶ ለብቻው መኝታ ተበጀለት። ህመሙ በሂደት ቀንሶ ጠፋለት። እጁን በእሚ በመታሸት አሳሳልፎ በእንቅልፍ ወደቀ። እሚ አጠገቡ እጁን በመደገፍ እና በመጠበቅ ስትተኛ፣ ብሩ ከጮለቅ ጎን እንደ አባት ሆኖ በትእዛዝ አደረ፨

ተገቢ ህክምና ለባቤ እየ ተደረገ፣ ወጌሻ ተቀጥሮ እጁም እየታሸ ሰውነቱ መሻሻል ከማግስቱ ጀምሮ አሳየ። ቤተሰቡ እፎይታ አጊንቶ ትንሽ ተነፈሰ። ወደ መጨረስ ሥራአቸው በጥንቃቄ ተመልሰው በአጭር ጊዜ ሁሉን እነ መስ አጠናቀቁ። ግማሽ ሜትር እማይሞላ ው መስታወት በተስተካከለለት ግድግዳ ወለል ላይ ሰምጦ ጣራውን ከፍ ብሎ ተገናኘ። የጓሮ በር በአንድ ቆርቆሮ ሲአበጅ፣ የፊቱ ግን ከአንድ ቆርቆሮ በግማሽ የዘለገ እና በግማሽ ቁመትም የሰፋ ነበር። በሩ እንደ ትልቅ ቤት መግቢአ ርብርብነቱን በእርጋታ በለጠጡአቸው ቆርቆሮዎች ስለ ተከወነ እና እንጨትዎቹ በእጅ መጥረቢአ ስለተላጉ ዓረንጓዴ ቀለም ሲጨመርብአቸው ድንቅ ዉበትን ከልስልስ እይታ ጋር ተሸከሙ። በአስራሁለት ቀንዎች ድካም ቤቱ ግድግዳዎቹ ቆመው ለእይታ ሲበቃ ሁሉም በመደመም እና መመሰጋገን ተመለከቱት። በክፍልዎቹ መሀል የነበረ አጭር ግድግዳ መሰል አንድሜት አጭር በር ተዘጋጅቶለት አንድ ፀጋት ላይ መሽሎኩን አመቻቸ። ከጓዳው ወደ ሳሎኑ እየተራወጡ ህፃንዎቹ ሲደሰቱ ሲጯጯኹ ዋሉበት። ወለሉ በስሱ በጭቃ ስለ ተለሰነ እና ቀደም ብሎ ስለደረቀ፣ እሚ በግል ወጪዋ ምንጣፍ አስገዛች። ቡና አፍልተው አጫጭሰው መስን በማመስገን ቡና ተፈላበት። አመሻሹ ላይ ጥቂት ወንበርዎች የተዋሰው ቤት ደመቅ ብሎ በተፈጥሮአዊ ግንቡ ኩራት ለብሶ፣ በዘለገ ቁመቱ ተኮፍሶ አስተናገደአቸው። እሚ የ አዘጋጀችውን መጠነኛ ዳቦ አቅርባ ፈንዲሻ እና ቆሎ ቀርቦ ቡናቁርስ ቀርቦ ሁሉም መመሰጋገን ተያያዘ። እሚ በማልቀስ ጭምር ሁሉንም አመሰገነች። የብሩ ጓደኛ ዮስ በሁለት ሦስት ቀን ማገዝ ተሳትፎ ስለ ነበር አብሮ ምስጋና እና ምርቃት ተቀበለ። ሁሉም በእየተራ መመሰጋገን ተያይዞ በመጨረሻ ለይፋ አገልግሎት ቤቱ መብቃቱ ከምሽቱ ቅኝት ኋላ ተረጋገጠ፨
እሚ ያገኘችውን የመጨረሻ ክፍያ በመጠቀም፣ መስም እያገዘ፣ ጥቂት ባህልአዊ ወንበርዎች፣ ወጥ ቤት ቁሳቁስዎች፣ እና መሀከል ላይ የቆመ ግድግዳ ላይ የነበረ ድንክ በሩን እሚከልል ሰፋ ያለፊቱ መስታወት የተገጠመለት መደርደሪአ ገዝተው አቆሙ። በሂደት ቤቱ ለመስተንግዶ እንደ ተዘጋጀ በመጨዋወት ሆነው አንዱ አዛዥ ሌላው ታዛዥ እየሆነ የማስተናገድ አቅምአቸውን ተለማመዱ፨
ናሆም ሦስት ልዩነት ፈጣሪ ቁምነገርዎችን ቀጠለ እና አከለ። ለእናቱ የመብልዎች ስነአሰራር አዘጋጅቶ ሰታነበውም ተቀምጦ ስተወፈልግ በአንድአቸው እንዲነበብ እና እንድትለማመደው አደረገ። እራሱ ስለ እሚሳተፍበትም ብዙ ሳያስጨንቃት ብቻ የሾርባ፣ ሀበሻ ፒዛ፣ ልዩልዩ መብልዎች ስነአሰራር አሰናዳ። ተጓዳኝ ምንአሌ በዉስን ቅጅ አትሞ በቀይ ላስቲክ አሽጎ አቀረበልአቸው። ተደምመው በማድነቅ ጨዋታ እና ቀልድ እየመራው መዝናናት እና መሞከሩን ከወኑበት። ባቤ በሳምንቱ እራስ በመቻል ግን በማንከስ እሚራመድበት እና እሚፍነከነክበት ሆነ። ጭራሽ ከጢዩ ጋር እሩጫ እና እርምጃ መሽቀዳደም ከወኑበት እና ሁሉ ተረገመ። ‘የልጅ ነገር!’
ቀጥሎ ቤቱን በከፍተኛ ማስዋብ ማራኪነት አላበሰው። በረንዳ። እንዲማርክ በነፃ እና ተዋበ መንገድ ገፅታ ቀባው። የጌጣጌጥዎች ሁኔታን በመቆጣጠር ይያዝ እንጂ የባቤ አንድ ድንቅ ሳቅ እና መንገድ የተሰኘ ስዕሉ ከመለጠፍ አልቀረም። ሳቅ እና መንገድ በዘለገ ወረቀት የተሳለ ሲሆን መንገድኛዎች በከፍተኛ ኹካታ እና ማስካካት እየተራመዱ መንደሩን በማወክ ሲጓዙ እንስሳዎች መብሉን በማቋረጥ በኩነና እና መጸየፍ ሲሚቱአሸው እሚአሳይ ነበር። ስዕሉ በሊቀደቂቅ ሰዓሊ ስለ ተሳለ የታዋቂ ሰዓሊ ያክል የሰመረለት ስዕል ነበር። ‘መንገድ እሚከለክለው የለም!’ በመብራትዎች መብዛት የቤቱን ድባብ መቆጣጠር እንዲቻል ቀለም ዉህድዎች ያገኙ መብራትዎች በተለየ በምሽት ድንቅ የመብራት ትርዒት ይሰጡ ነበር፨
ሦስትኛ ደግሞ ናሆም የገበያ ድር በመመስረት ልዩልዩ ተግባርዎችን ከወነ። በ ከፍተኛ ዘዴአማአዊነት የ ታዳሚዎችን ቀልብ ለመሳብ ማስታወቅያዎችን በመለጠፍ እና ሰውዎችን በማነጋገር ይህን ሙከራ አደረገ፨
ወደ ጋሽ ተሻገር በመመላለስ በማበብ እሚገኝ ሰብልዎቹን በመንከባከብ እና በላጭ አስተዉሎት ከተሞክሮ መጋራት ጋር እየከወነ ሰነበተ። በመጨረሻ፣ ሃምሌ አጋማሽ ላይ ቤተመብሉን ለአገልግሎት ክፍት አደረጉ፨
በ ሂደትዎች የመለመዱ ሁኔታ በዝቶ፣ በከተማው ዕዉቅ አዲስዎች በ መሰኘት ብዙ ጎብኚዎችን አስተናገዱ። በወሩ ማብቂአ፣ ከእዉቅናአቸው መትመም የተነሳ የከተማው አስተዳደር ንግድ ፈቃድ እንዲአገኙ አስተያየት ለማቅረብ ጉብኝት በተላኩ በአለሙያዎቹ አደረገ። ናሆም ይህን ለመከወን አስፈላጊ ሁኔታዎችን ከእናቱ ጋር ፈጽሞ ግብር ከፋይ ነጋዴነቱን እሚ እንድትቀበል አደረገ፨
የ እሚ ልብ በመገረም እና ትጋት ሆኖ ማገልገሉን ተያያዘ። በቤትአቸው የተከፈለ ኑሮ ሊቋቋም ሆነ። ቀን እሚንጠባጠብ እንግዳ በማስተናገድ እሚ እና ናሆም ሲውሉ የቀረው ቤተሰብ በቤቱ ይዉል ነበር። አዲስ ድባብ ለቤተሰቡ ሆኖ አዲስ መስመር ለእሚ አዲስ ተሞክሮ ለናሆም ተቋቋመ፨

በ ቤቱ የተለያዩ እንግዳዎች ይመላለሱ ነበር። የክረምት ተማሪዎች፣ መምህርዎች፣ ከመንደሩ እሚመላለሱ የመስሪአቤትዎች ሰራተኛዎች፣ ተገልጋይዎች፣ መደበኛ ዜጋ ው፣ ወዘተ. በጥሩ መስተንግዶ ተደስተው ስለ እሚሄዱ በትሁት አያያዙ እና አልሚ እንዲሁም ርካሽ መብሉ ተማማርከው መመላለስ ያበዙ ነበር። ጭራሽ በእቃዎች ተደርጎ መብል ወደ ዉጭ እንዲሄድ እሚታዘዝ መሆኑ እየ ተለመደ መጣ፨
ከ እሚመላለሱ ደንበኛዎች መሀል አንድ ሰሞን የነጭዎች ቡድንም ተገኘበት። አራት ነጭ ግለሰብዎች እና አንድ ምዕራብ አፍሪቃአዊ በአንድነት ከአስተርጓሚአቸው ጋር በምሣ ሰዓት አቅራቢአ ሲገቡ ናሆም እና መስቤ አንድ ወንበር ይዘው በመቀመጥ ይጨዋወቱ ነበር። ስድስቱም እንግዳዎች አንድ ክብ ጠረጴዛ ላይ ቡድን ሰርተው ተቀመጡ። ናሆም በመቀመጡ እረድቶ እሚፈልጉትን ለመታዘዝ ፊትለፊትአቸውበምን ቋንቋ እንደ እሚናገር ግራ ገብቶት በትህትና ጎንበስ ብሎ እጅ በመንሳት ብቻ ቆመ። ከግዕዝ፣ እና ኦሮምኛ ጥቂት ሙከራ በዘለለ አማርኛ እና እንግሊዝኛ አቀላጥፎ ይችል አለ። ፈረንሳይአዊ (ፍሬንች) ደግሞ ገና በመጀመር ላይ ስለነበር ከአጭር ሰላምታዎች በቀረ እሚችለው የለም። ‘አንድ ቋንቋ ማወቅ አንድ ዓይን እንደ መያዝ ነው። ሁለት ቋንቋ እንደ ሁለት አንጎል ነው።’ እሚችሉትን ቋንቋ ስለእማያውቅ በድፍረት እንግሊዝኛ ለመናገር ሲል አስተርጓሚ ው በ አማርኛ
“ብዙ አይፈልጉም! ለ ማረፍ ነው ከ እዚህ ቢሮ ጉዳይ ስለ አልጨረሱ የመጡት!” ብሎ ሊሸኘው ተናገረ። ነጭዎቹ መፃተኛዎች ስለ ሆኑ ምንም ለመጠቀም ሳይገደዱ ለማረፍ ብቻ መፈለጉ ናሆምን አላበሳጨም። ‘እንግዳ ተቀባይ መሆንአችን ከገጠር ወደ ከተማ ለእምንሄደው ባይደረግም፣ ከውጭ ሃገር ወደ እኛ ለሚመጣው ግን አለቅጥ ይደረግ አለ፤’
ብቻ በደስታ ፈገግ ብሎ ለመመለስ ሲል አንዷ በሠላሳዎቹ እድሜ አጋማሽ እምትገኝ ወፈር ያለች ዳለቻ ሱሪ እና ነጣ ያለ ስስ ሹራብ የተጫማች ወርቅአማ ፀጉሯ በትከሻዋ ላይ እንደ ደረሰ ቆም ያለ እንስት ጓደኛዋ ጮኽ ብላ ተናገረች። “አይ ቲንክ አት ሊስት ዊ ማይት ዋንት ቱ ቴክ ኧ ኮፊ ኦር ሰምቲንግ፤ ሊድ? ሌዲያ!” ሊድ ቀጠን ብላ ተመሳሳይ ቀዝቀዝ ያሉ ቀለምዎች ያሉአቸው ልብስዎችን የለበሰች አጠር እምትልም በአለ ጥቁር ፀጉር ነጭ ነበረ ች። መልስ ከመስጠት ዋ ቀድሞ “ኢት ኢዝ ክሊን ሆም…እ?” ሲል ተርጓሚ ው በአነሰ ድምፅ ተናገረ። ናሆም የእሚአየው የድምፅ ልዩነት ገረመው። ተመልሶ መስ ጋር ቁጭ ብሎ መስን በመመልከት ጆሮዎቹ የሰጡት የድምፅ ልዩነት ገረመው። ነጭዎች እና ብዙ ጥቁር ሰውዎች ኢትዮጵያአዊ ካልሆኑ ድምፅአቸው በከፍተኛ ጉልበት ከጉሮሮ በተፈጥሮ እሚወጣ ነው። የአመጋገብ እና ያትኩሮት አቅም ልዩነትአችን እንደ ሆነ አሰበ። መልሶ ደግሞ በባህል ሀበሻ ስለ እሚንሾካሸክ ድምፁ በትንሽ መጠን በ መራመድ እንዲወጣ ስለ ለመደ እንደ ሆነ አሰበ። መልሶ ደግሞ የነዎጮች ቤቶች እጅግ እረዣዥም ጣሪአ ያሉአቸው፣ ሰፋፊ ቤትዎች እንደ ሆኑ እና ጮኽ ከአላሉ መነጋገርአቸው እንደ እማያሰማማ እና በ ቤተዘር (ሃቢታት) መለያየት እነወደ ሆነ አስተዋለ። በነፃነት ጮኸው እንዲአድጉ መደረግአቸው እና ያለመገደብ ባህሉ ከእኛ ስለእሚሻል እንደ ሆነ መልሶ አዘመመበት እና ሃሳቡን አስተዋለ። ወይ ደግሞ የዘረመል ተፈጥሮ ሊሆን ይችል አለ በማለት ደግሞ አሰበ። ብቻ አንድ አመክዮ አለ ማሰስ አይቻልም። የነጭዎቹ ድምፅ ቱሽቱሽ ሽለው ሲነጋገሩ እንኳ ለጣሪአ ያሰጋ ነበር። ሀበሻ ግን ሲጮኽ እንኳ አይሰማም፨
ናሆም አሁንም በዝግታ ድምፅ ለ መስ ልዩነቱን እንዲአስተውል ጋበዘው። መስ አስተዉሎ ብቻ ሳይሆን ከ ተሞክሮ ሃሳቡን ጨምሮ በዘለገ ድምምፅ አጋራ። “አዲስአበባ በ ታክሲዎች ብዙ ጊዜ ይገጥሙኝ ነበር።” ይህን በዘለገ መደበኛ ድምፅ ሲመልስለት ናሆም በ ለ ሆሳስ መጠየቁ አሳቀው። ነጭዎቹ አማርኛ አይችሉም። “እና ታክሲው ዉስጥ ከ ሀበሻዎች ጋር ተቀምጠው ሲንሾካሾኩ በሩ ላይ ከእሚጮኸው ወያላ በላይ ይሰሙ ነበር!” ናሆም ሣቀ። “የስነልቦና ጉዳይ እንደ አለበት ጥርጥር የለውም!” መ ቀጠለ። “አመክዮው ደግሞ ምንም ሳይመስልአቸው የፈለጉትን ሰማም አልሰማ ሳይሉ ሲአወሩ ስለ እምትመለከት ነው። ሁለትኛ ደግሞ እማይመለከተው ሰው አጠገብአቸው ተቀምጦም ምንም ቢጮኹ አያደምጥም። በእራስህ አኗኗር ብቻ ተጠምደህ አጠገብህ አዉሬ ቢቀመጥ አለ መመልከት እና አብረህው መጓዝ ድረስ መድረስ አለብህ። የእነ እርሱ ዓይንዎች መሰብሰብ እና ከቶ ቀና ብሎ አለመመልከት ያን ያክል ነው። ነገር በዓይን ይገባ አለ። ይህ የሰው ልጅ ፈተና ነው። ነገርግን ያልሰለጠነ ማህበረሰብ ዉስጥ በሰው እና ቁስ ላይ ይፈጠጥ አለ። መፎካከር እና መወዳደር በስነልቦናአችን ይሰርግብን አለ። የተመለከትንው አንድምታው ተገልጦ በልቦናአችን አይፃፍም። በ ማፍጠጥ ስናልፍ በስዉር አንደምታ ግን የመፎካከር እና የማነስ ስሜት ይወርረን አለ። የተደበቀ ማንነትአችን በ ሰውለሰው ግንኙነት ከመሳብ በቁስ እና ወጪ ወራጅ ማፍጠጥ ይሰረቅ አለ። ስለ እዚህ ከእራስ ማምለጥ እና ከ አካባቢህ ድባብ መዉጣት እና ማፈንገጥ እንለምድ አለ። ሲቀጥል ደግሞ ዋናው ያለመሰልጠን ነገር ይከሰት አለ። ሰውን በሰውነቱ አትረዳም እኛ ጋር። በማፍጠጥ ሁሉን ስትገመግም ነው ሱቅ እንኳ ወጥተህ እምትመለሰው። ቀና ሳትል መጓዝ እና ሸምቶ መመለስ የተዓምር ያክል አቅም ይሰበስብልህ አለ። ምክንያቱም ልብህ ከ ማ እሻል አልሻል ብሎ ከቢሊየን ወጪ ወራጅ በስዉር ልቦና አልተፎካከረም። ምክንያቱም አልተጨነቅህም።”
“ነገርግን፣ እኛ..” ወደ ነጭዎቹ ተመለከተ እና ፈገግ አለ። ናሆምም የቀረው ግልጥ ስለ ነበር በመሰል ፈገግታ ነጭዎቹን አየት አደረገ። “እኛ ያኗኗር ተሞክሮ ለልጅዎች ሰጥተን መልካሙ ትዉልድ እንዲፈጠር አንተጋም። የእኛ ትውልድ ኖሮ አላፊ ነው። ከዜሮ ጀማሪ ደግሞ መጪው ትዉልድ ይሆን አለ። እንጂ ሀበሻ በዓይንዎቹ እንደ ቀረው አለም አደጋ እሚሸምት ነው። ወጥቶ በሰው ሰውነት ላይ እና ቁሳቁስዎች የአፈጥጥ እና ስነልቦናው ይሽመደመድ አለ። ሌላው አለም ይህን በአንድ ወዉልድ ሲገነዘብ ቀጣይ ትዉልዱ ዓይንዎች እንዳይፈጠጡ መክሮ ዘክሮ፣ እራሱም እየመራ እማያፈጥጥ ትዉልድ ፈጥሮ፣ ትዉልዱ አቅሙ በጉያው የተወሸቀ ከባድ ይሆን አለ። ሰው ቀና ብሎ ስለ እማይመለከት እፍረት የሌለው ቀና ስብእና ይይዝለት አለ። አፍጣጭ ግን በሰራቂ ዓይንዎች ከ ሷሁሉ ሲወዳደር ስለ እሚኳትን፣ ከሁሉ ስትወዳደር ደግሞ አንድ ነገር ላይ እበለጥአለሁ ማለትህ ስለ እማይቀር የበታችነት ስነልቦና ይጥልህ አለ። ስለ እዚህ ሁሉን ለማስደሰት እና በታችነትህን ለማካካስ ትራወጥ እና ማንነትህን ታበላሽ አለህ። ምክንያቱም ማንም አይጨነቅም። በግልህ ግን ተጨንቀህ ሰው እሚኮንንህ መስሎህ በ ግለ-ወጥመድ ትወድቅ አለህ። ይህ አምራች ዜጋ እንዳይኖረን ሸሺ እና በግሉ እሚአፍር ስነልቦና እሚነዳው ትዉልድ እንድንፈጥር ያደርገን አለ። መልክ እና አቋቋም አምላከከ ትዉልድ ይፈተካን አለ።” መስ ማወዳደሩን እና ስነልቦናትንታኔ (ሳይኮአናሊሲስ) ሲከውን ናሆም በ መደነቅ ከ ነጭዎቹ መኖር ጋር የ ተፈጠረ ድባብ ጋር በማዋሃድ ማድመጡን ቀጠለ። “እና ነጭዎች ቀናዎች አዎንታአዊነት እሚአሳዩህ እሚሆኑት ወላጅዎችአቸው የሰው ዓይን ነገር ይገባበት አለ ብለው ዓይንዎች እንዳያፈጥጡ፣ ወጥተው ብዙ አገልህሎት አግኝተው ሰላምአዊ ሰልፍ ከውነው ሲመለሱ ግን ያፈጠጡበት ስለ ሌለ በ አልኮመሸሸ ስነልቦና ስለ እሚመለሱ እና በመወዳደር ስሜት ሰው ስለ እማያንቋሽሹ ግልአቸውም ጤነኛ ስነልቦና ስለ እሚይዝ ነው። ከአዉሬም ይኖሩ አለ። ይህን ባህል ግን እኛ አልመሰረትንም። ማን እንደ አለ ሆቴል እሚገባ እንኳ ሳይቃኝ አይቀመጥም። ታክሲ እሚገባ ገብቶ የተቀመጠ ላይ ሳያፈጥጥ አይቀመጥም። የተቀመጡትን ቆጣሪ ይመስል። የትም ስብሰባ ፊት መቀመጥ ይፈራ አለ። አፍጣጭነት ስላለ እንደ እሚፈጠጥብህ ታውቅ እና አይፈጠጥብኝም ብለህ ታፍር አለህ። ከምእራብ አፍሪቃ እሚመጡ እንኳ ይህን ባህል እየተዉ እድገትአቸው አብሮ እየአሻቀበ ታስተውል አለህ። ትልቅ ምስጢር አለው ብቻ። የሃገር እድገት በ ዓይንዎች በ አለ ማፍጠጥ ይቀጣጠል አለ ሲባል ግን ስነልቦናትንታኔአችን ከቶ እማይነካው እና ለታዳጊው ትውልድ እማይወረስ ጥበብ ሆኖ የአልፍ አለ። በወሬ ብቻ እሚቀር ትዉልድ የሆንነው በመሰባሰብ ወቅት ማፍጠጥ ስለ አለ መሰባበሰብ እና አንድ ነገር ማድረግ ስለ እማይቀናን እና ስለ እምንፈራ ነው። እድር፣ ለቅሶ እና ሰርግ ባይኖር ሃበሻ ተሰባስቦ አይታይም ነበር። ማፍጠጥን ይፈራ አለ። ካልተሰባሰበ ደግሞ ሰው ሃገር አይገነባም። ሰው በማምለጥ ሲኖር ህብረትአዊ አሰራር ይጠፋ አለ። በ ህብረት ከ አልተሰራ ደግሞ የት ይደረስ አለ? ሃገር መገንባት ቀርቶ ለግልህ መሆን አታካች ይሆን አለ። ኑሮ ደግሞ ለእኛ የአ ነው።”
መስ በተናገረው ዉስጥ ብዙ ሃሳብዎች እንደ ነካካ ናሆም አስተዋለ። ዉሃ አምጥቶ ለሁለቱም ቀዳ እና አፉን እንዲአርስ ጋበዘው። የተገረውን በማስተዋል ሊአብሰለስል ትንሽ አፍታ ወሰደ። ‘ህብረት ነው እሚነገድ፣ እሚሰራው በእርግጥ፣ ማፍጠጥ እንዴት ይራቅ ታዲአ?’
“ግን ሀበሻ ተሰባስቦም አለ ማፍጠጥ ቢለምድ ማህበር አይሆንለትም። ምንም የለንም። ድሃ መናጢ ነን። ግን ለመስራት ተሰባስበን አተያየቱ የደበረን ሰው ካለ እናኮርፍ አለን። ከፍተኛ ቢባል እማይገለፅ አትንኩኝ አትዩኝም ባይነት አለብን! ወርቅ ቢነጠፍ እንቢ ብለን ወደ ፋንዲያ እምንሸሽ ነን፣ የምንጊዜውም አንድኛ የኢትዮጵያ ገዳይ እና አንድኛ ጨካኙ ዜጋ እንደ ነገረን።”
መስ የናሆም ሃሳብን አድምጦ ፈገግ አለ። “ልክ ነህ! የአስተዳደግ ጉዳይ ነው። እምትለምደው መሸሽን ነው። ወደ ፊት መዉጣትን አይደለም። አንድ ጊዜ የህግዘብዎች እጅኳስ ዉድድር ስንከውን የሆነውን አልረሳውም!” መስ በሃሳብ ነጎደ። ፊቱ ላይ ስስ ፈገግታ ጣል አድርጎ መናገሩን ቀጠለ። “ተሰብስበን በጎራ እየደገፍን ስንዝናና አንዱ ቡድን አስቆጠረ። አንድ ዋ ወጣት ህግዘብ ተነስታ በመጮኽ ጨፈረች። ሁሉም ጨፈረ። ግን ደስታው በእሷ በለጠ። ለካ ወንድሟ ነበር ያስቆጠረው። ከእሩቅ የነበሩ ሁለት ስራ ፈትተው የተቀመጡ ህግዘብዎች ጮኹባት። አንዱ በከፍታ ድምፅ ‘ወይ አታምር ወይ አታፍር!’ በማለት ተቆጣት።” ናሆም በሣቅ ፈነዳ። እየተሣሳቁ ለጤናአቸው በመጨነቅ ሁሌ እንደ እሚአደርጉት ንፁህ ፈሳሽ መዉሰዱን ቀጠሉ። መስ ሳቁ ጋብ ሲል ነጥቡን ሊጠቀልል ጉሮሮውን አከከ። “እና! አስተዳደግ ለ መልክ አምልኮ ሰጥቶ አንዱ የስነልቦና ቀዳዳአችን ሆኖ አለ። በመሰብሰብ መተቻቸት እና መብጠልጠል ያለው ከእዛ ይመስለኝ አለ። ማንም ቆንጆ ያሻውን ይሁን ትንሽ አስቀያሚ የሆነ ይጥፋ እሚል አስተሳሰብ እንደ ማህበረሰብ አለን። ቆንጆ ከፍተኛ ተሰሚነት አለው። አመክዮ አፈርድሜ በልቶ አለ። በእዚህ ግን ቁንጅና ዋጋ ይጣ ማለቴ አይደለም። ግን እንደ ሠለጠኑት ለመሰልጠን ሰብእአዊነት ሊአንፀን ይገባ አለ። በእዛ ደግሞ መተቻቸት እና መተፋፈር ትተን በጋራ ችግር ወደ አንድነት ማፋፋም መመለስ አለብን። የእማይመቱት ልጅ ቁጣ እንደ እሚአስለቅሰው በመሰብሰብ መስራት ማደግ ስላልለመድን ገና በመመተያየት ተከፋፍተን እንለያይ አለን፤ ብንሰባሰብም።”
“እሺ ስነልቦናተንታኙ! ግን ለዘረዘርከው መፍትሔው ምድነው?” ናሆም እንግዳዎቹን መልከት አድርጎ እሚፈልጉት ካለ በመሰለል ምንም ምልክት ስለ አልተሰጠው በመመለስ ጠየቀ። “መፍትሔው አንደ የፀሐይግባት ላይ ያወራናት ነገር ናት! ትልቅ ነው የተናገርከው። ሰው በግሉ የተሸበበ የሆነው እና ፋንድያ እሚቀናው የሆነው መገሸሽ ያለበት አኗኗር ስለ አሳደገው ነው። ስለ እዚህ ሰው በመሆንህ እልፍ በቂነት እንደ አለህ እንድታውቅ ተደርገህ ማደግ አለብህ። አኗኗርም ያንን እየአንፀባረቀ ደመቅመቅ ባለመሞጋገስ ዉስጥ እና ሙቅ መስተጋብር መኖር መልመድ አለብን። ፍልቅልቅ ማህበርአዊ ሂወት እንደ ሃገር መብዛት አለበት። ይህ ወደ አንድ አንጎል ሃገሩ ሁሉ እንዲመለስ ይፈቅድ አለ። ፀሐይግባት እና የጊዜ አገነዛዘብ፣ የተፈጥሮ እና ሰውሰራሽ መስህብዎች መጎብኘት እና መማረክ ማስለመድ አለብን። እንደ ቀረው ዘመንአዊ ማህበረሰብ። ለምን? ምክንያቱም ይህ የመዘን ቀመር ነው። ከእዛ ዉጭ መዘን የለም። እንደ አልክኝ በመስህብ መማረኩ ነብስን ከያዛት አዚም እሚአላቅቅ ነው። ሰው የመሆን እና የጊዜ ዋጋ እንደ እማይገታ አስመለክቶ አናሳሽ የአደርገው አለ። በብሔር በሃገርህ ከመተራረድ ወደ ሰብእአዊነት ብቻ ሳይሆን ወደ ሁለንተናአዊ አሳቢነት ትመለስ አለህ። ለእንስሳዎች መከራከር ትጀምር አለህ። የተፈጥሮ ቅኔን መገንዘብ አለብን ነው በአጭሩ። በተፈጥሮ ቅኔ ወርቁ ከታየህ እንደ ዲአቆን ዳንኤል ክብረት”
“ሙአዘ ጥበቡ?” ናሆም አቋረጠ እና ማዕረግ አከለ። መስ ተስማምቶ አናቱን ነቀነቀ። “ሰው በአራት ስብእና አለ ብሎ በአዉሬነት ደረጃ እንደ እምንኖር ነግሮን ነበር። ወደ ሰብእአዊነት ደረጃ ለመድረስ ተፈጥሮን ማሰስ አለብን ነበር የአለው። ተፈጥሮ ቅኔዋ እንዲገባን ነበር ያሰበው። ሲገባን አንድ ነን። ሁልአችን በአንድ ችግር እና ተፈጥሮ እምናልፍ ስነፍጥረትአዊ (ክሪኤሽን) ተጓዥዎች ነን። ከቶ መከፋፈልን አንከውንም። ተሰብስበን መስዳቱን አንፀየፍም። እና በማወቅ ዉስጥ ባህል መለወጥ አለ። እንጀራ ለመብላት ማወቅን ማውገዝ አለብን ማለት ነው እንግዲህ! ለመብላት ሰው መሆን ከበቂ በላይ ነው። ግን ዕዉቀትን እና መማርን፣ ማገልገልንም በእንጀራ ሂሳብ ቀይረንው አዉሬነት ማዕረግ ሰቅዞ ቅርቃር (ዴድኢንድ) ዉስጥ ከትቶን አለ። መዉጫው ባህሉን መቀየር እና አንድ ወዉልድ ማሰልጠን ነው። አመለካከቱ ወደ ሃቅ እና ሰብእአዊነት እንጂ ወደ ቆሻሻው፤ ማር እና መርዝ የሆነው በዕዉቀቱ ገጣሚው እንዳለው ከመልክ መመልከት አዚም መዝለል ከ አልቻልን ለ እኛ ማደግ የለም። ዐዋቂዎች እና መንግስት በትዉልድ ማበልፀግ ሃገር መበልፀግ አለ ብለው አምነው መታተር አለብአቸው። የአኔ ተስፋ አለ።”
መስ ሃሳቡን አስቀምጦ በ ንዴት አናቱን ነቅነቅ ሲአደርግ ናሆም በመገረም ሆኖ ማድመጡን እና የገባበት የመገለጥ መስመር አንድ መስመር ላይ እንዲተወው በመጠበቅ ነበር። መልሶ ወደ እራሱ ገባ እና “መልሱ በ እዚህ ዉይይት ሳይሆን በ ትግበራው ነው” በለሆሳስ ለእራሱ ተናገረ። እራሱን ነቅነቅ አድርጎ መረዳቱን ከወነ። ‘ወርቅ ይገባኝ አለ እሚል ዜጋ ለ ማፍራት ፍቅር ለታዳጊዎች አንንሳ። ሰው መሆን ለመጨረሻው ክብር እና ማዕረግ በቂ መስፈርት ነው! አምላክ በአምሳሉ ሰርቶን ስናመልከው በእርግጥ ድሃነት ማፍቀር ከልክሎን መልክን መመልከት አዋርዶን አለ፤’
መስ ከዉሃ ብርጭቆው ላይ የነበረችውን ጨርሶ አዲስ ከጆኩ ሞላ። ናሆም ወደ ነጭዎቹ ሲመለከት ተርጓሚአቸው እና እነ እርሱ ሲወያዩ አስተዋለ። ትልቁ ድምፅአቸው በሀሃድ ይደመጥ ነበር። የመጡት በከተማው ለእሚሰሩት የአፈር ምርመር ሲሆን የአንድ ተግባሬት ልዑክዎች ነበሩ። ጥቁሩ ወጣት እና አንዱ ሌላ ወጣት ነጭ ተማሪዎች ሲሆኑ አብረውአቸው ተለማማጅዎች ነበሩ። በአካባቢው የነበረውን የዞን ግብርና መስሪአቤት ለማናገር መጥተው ገና ፋሲካይት መድረሳቸው ነበር። በመስሪአቤቱ ኃላፊው ለ ምሳ ገና አምስት ሰዓት ስለ ወጣ እንደ ደረሱ ማግኘት ሳይችሉ ከ ተመለሰ ብለው ጠበቁ። ምሣ ሠዓቱ እስኪአልፍ ለመታገስ ሳይችሉ አረፍ ብለው ለመመካከር ነበር ወደ እነ ናሆም ደች የመጡት፨
አሁንም ተርጓሚ ው ቤቱ ምሣ ከአለው ለመጠየቅ እንደ እሚችል እና ከስምንት ሰዓት በፊት አገልግሎት እንደ እማይጀመር ለማስረዳት ሲደጋግም እነ እርሱ ደግሞ ምሣ በተሻለ መስተንግዶ ቤት መመገብ እንደ እሚፈልጉ ተወያዩ። ሌላው ጎልመስ ያለ ነጭ ወጣትዎቹን አነጋግሮ ቢአንስ ቡና መጠጣት እና ማየት እንደ እሚሻል ተነጋገሩ። ናሆም ይህን አድምጦ ተጠጋ። “ዊ ሃቭ ኧ ቬሪ ጉድ ኮፊ! ዱ ዩ ኦል ዋንት ኤ ካፕ?” ብሎ ጠየቀ። ፈገግታ አክሎ ሲናገር ተስተናጋጅዎቹ ተደስተው “ኦ ያ!” በማለት መለሱ። አስትርጓሚው ተበሳጨ። “ቡና አልፈለጉም ነበር!” በመቆጣት ናሆምን ተመለከተ እና ተናገረ ው። ናሆም በዝምታ ተመልክቶት ወደ እሚ ሄዶ ለነጭዎች እሚሆን ቡና አላት። ቡናው በከፊል ሣሎን ወጣ። እዛው ቶሎ ተፈላ። የእጣን መጫጫስ እና ፈንዲሻ መቅረብ ነጭዎቹን ማርኮ ቀረበ። በቅመማቅመምዎች እና ከጎኑ ጤናአዳም የተጋደመበት ቡና በቀጥታ ተንቆረቆረልአቸው። ሃገሩን በቡና መስተንግዶው እንደ እሚአቅ ጎልማሳው አንስቶ እየተጨዋወቱ በደስታ ጠጡ። ናሆምን ጠርቶ በእንግሊዝኛ ስለ ቡና እና ባህሉ ተጨዋወቱ። በመሣሣቅ አድምጠውት ስለ ምሳ አዋዩት። በከፍተኛ ጥንቃቄ ሁሉም እንደ እሚሰናዳ እና ደግ መስተንግዶ እንደ አለ አስታወቀ። ለመሞከር ተስማምተው ሁለት የአትክልት ሾርባዎች በደንብ ተንሰርስሮ እንዲመጣ አዘዙ። ናሆም በታዘዘው መልኩ አሰርቶ አቀረበ። የቅመማቅመምዎች ዕቃዎችን ሁሉ በመጠየቅ እየአዋሃዱ ከብዙ አትክልትዎች የተዘጋጀ ሾርባውን በህብረት ቶሎ አጠናቀቁት። ወዲአው ሁለት እንዲደገም እና ዳቦዎቹ እንዲበዙ፣ አብሮ የሽሮ መብል እንዲቀርብ ጨምረው አዘዙ። ንፁህ ዉኀም አብረው በመጠቀም በመሰል ፍጥነት መብሉን ፈፀሙ። የእሩዝ እና አትክልትዎች መብል ደግሞ ናሆም አብራርቶ ከአስመረጠው እንዲጨመር አደረጉ። በተለየ ትእዛዝ ደግሞ ስጋ በቲማቲም እና አትክልትዎች ተጠብሶ እንዲመጣም አደረጉ። በምርጫዎችአቸው መሰረት ሁሉንም እሚ እና ናሆም አስተናገዱ፨
በመስተንግዶው እረክተው በቆይታአቸው ወደ እዚህ በመመላለስ ሊመገቡ በመወያየት ዳግም ቡና በእሚ ተጋብዘው ሲጨዋወቱ ቆዩ። ናሆም እና መስ ስለ ተርጓሚው መናደድ እና ደስተኛ አለ መሆን አንስተው መወያየት ጀመሩ። “ብዙ ዓመት እንግሊዝኛ ተምረን ግን መረዳቱ ላይ የአንድ ዓመት ልምድ ያለን ያክል እምንሆን ብዙዎች ነን።” መስ ሃሳቡን ሰጠ። መስ እንኳ በግሉ የናሆም እገዛ ደግ መጠን ላይ በቋንቋው ክሂሎት አድርሶት ነበር። እንደ ትምህርት ባይሰጥ ብለው ስለ ቋንቋው ስኬትአማ አለ መሆን ተነጋገሩ። “በተለየ መንገድ ብናጠናው ቶሎ እንደ ማንኛውም ቋንቋ እንለምደው ነበር። እንደ ትምህርት አይነት ግን ብዙ ዓመት አጥንተንም በእሚገባ አንቀዳጀውም።” ናሆም ይህን ሲናገር መስ ግን በአስጎብኝነት ጉዳይ ላይ አንድ ትዝታ ገጥሞት ሲአስብ ነበር። ወደ ናሆም ዞሮ ፈገግ አለ። “አሁንም በህግዘብነት ሥራውን ከመጀመር ቀድመን ስለ ሃገር ፍቅር እና ታሪክ ለማጥናት እንድንችል ቤተመዘክርዎች ሲአስጎበኙን ነበር። እና እንጦጦ ቤተመዘክር ስንገባ ቀደም ብለውን የነጭዎች ጎብኚ ቡድን ፊትአችን አዝግመው ነበር። ለሀበሻ ጎብኚ ግን እማያብራሩ ነበሩ። ‘ሂድ ትኬት ቁረጥ’ ይሉህ አለ። ቆረጥህ። ‘ግባ እና ዞረህ ቶሎ ዉጣ’ ይሉህ አለ፨
ለእኛ ገለፃ እሚአደርግ አልነበረም። አንገቱ እስኪበጠስ በመጮህ ብዙ ለነጭዎቹ እሚአብራራውን፣ እኔ እንግሊዝኛዬ ምስጋና ለአንተ ደግ ስለነበር ደፍሬ ተቀራረብኩ” መስ ፈገግ ብሎ ናሆምን በማመስገን ዓይንዎች ሆኖ ተመለከተ። “እና በባዶ ክርክር ከእሚዞረው ቡድኔ ፈንጠር ብዬ ማብራሪአ ለመስማት ከነጭዎቹ ቂጥቂጥአቸው ስር በመደበቅ ስከተል፣ ድንገት አጭሩ አስጎብኝ አንገት አስግጎ ተመከተኝ። ‘አንተ! ዞርዞር ብለህ በግልህ ተመልከት! አልተመቸኀቸውም!’ ብሎ በኩርፊአ ተናገረኝ።” ናሆም ከት ብሎ ሣቀ። ሦስት እንግዳዎች ሲመጡ ምሣ በመታዘስ ዉሃ ጋብዞአቸው ወደ ሣቁ እየተመለሰ ተቀመጠ። “እና በግልህ ቃኝተህ ተመለስህ?” ናሆም ሣቁን ቀጥሎ ጠየቀ እና ጨዋታውን አስቀጠለ፨
“ሳላስበው በእንግሊዝኛ ተናገርኩ። ‘አይ አም ኦኬ’ አልኩታ በደመነብስ እና ትዝብት። የሚመልሰው አጣ፤ አየት አድርጎ አፈጠጠብአቸው። ምንም አላሉም። እነእርሱም ማብራሪአውን ይጠብቁ ነበር። አብሬ እያደመጥኩ ዞርኩ እልህ አለሁ።” መስ የአገልግሎት ክፍያውን አስመስክሮ ከወጣ በኋላ ሌላ ጉብኝት በግሉ ሲከውን ግን በአስጎብኚዎች እንደ ተደሰተ አስታወሰ እና ጨዋታውን ናሆም መብል አቅርቦ ሲመለስ ቀጠለ።
“አንኮበር ስሄድ ‘ማርታ እባላለሁ። አስጎብኝህ ነኝ’ ብላ ለ ብቻዬ ሆኜም፣ ሀበሻ ብላ ሳትንቀኝ ሠፊውን የምንይልክ እልፍኝ ፎቅ አዙራ አስጎበኘችኝ። ደግ ነገሮች ይነግሩህ አለ በእርግጥ። ለእማያነብ ሰው ደግሞ ደህና መረጃ ከመስህቡ ጋር ማግኛ ይሆን አለ። ታሪክ በቤተመዘክር እይቱ ይጥምህ አለ። አስጎብኚ ደግሞ በተቀነጨቡ እቅጭ መረጃዎችዠ እይቱን ያግዙልህ አለ።”
“ብቻ ከአምባ አናት ላይ ለደህንነት ሲባል እንደ ህፃን ቁንጮ ጉብ ያለችውን የቤተመንግስቱን ጓሮ ለመመልከት ስዞር ግን የተራበች ሰስ ለእይታ በአጭር ክፍል ዉስጥ ተይዛ አየሁ። ሳር በመቀነጣጠብ፣ በግሌ መጎብኘቱ ፈንታ፣ በግሌ አብልቻት ሄድኩ። አንዷ እመስት ‘ምሣ ሰዓት ዋ አልደረሰም’ ብላ ብትቆጣኝም አላስችል ብሎኝ ብቻ ‘አይ መቆያ ነው!’ በእሚል ቅጠላቅጠል ጨምሬ የሽቦ ክፍተቱን በ መጠቀም አብልቼ ጓደኛአልባ ለ ሆነችው ድንቅ ሰስ ዉለታ ዋልኩ።” ናሆም ስለ አጋጣሚው ተገርሞ አድምጦ ብዙ ያለ መጠንከር በይፋ ሥራዎችአችን ሊኖሩ እንደ እሚችሉ ልብሳለ። “ብዙ ጎብኝተህ አለ አይደል?” ከአስጎብኚ ወደ ጉብኝት ተመለሱ። መስ የማወቅ እና የመነሳሳት እኩል ስሜትዎች ስለ ነበሩት ትንሽ በህግዘብነት ሀገሩን የመንቀሳቀስ እና በ ገባበት ምን ምርጥ ነገር፣ ታሪክ እና ባህል አለ ብሎ ይጠይቅ ነበር። በጉብኝቱ፣ የዓለምን እና ጊዜን መዳፍ ጨበጥ ያደረገ ያክል ይሰማው አለ። ከሩቅ እድሜዘመን የነበረ ስልጣኔ እና ኑባሬ መጨባበጥ ነው ብሎ ይረዳ ነበር። ከአለፈው ዘመን ለመነጋገር ቢያንስ ማጥናት ይሻ አለ። ግን መጠነኛ መጨባበጥ በጉብኝቱ መከወን ሲቻል አስተዉሎ ስለነበር መጎብኘት በቻለ አጋጣሚ ሁሉ አደክምም አይሰንፍም።
“እኔ እንኳ አንዴ አዲስአበባ ብቻ ነው ለመጎብኘት የሄድኩት። በአስረኛ ክፍል ሌማሪዎች ህብረት ስለ ነበር ብዙ ጊዜም አላገኘሁም። በአጋጣሚ የአብዮት ሃውልት ለኩባ መታሰቢያ የተሰራውን እና አንበሳ ጊቢ የተራቡ ከሲታ አንበሶች ተኝተው አሳይተውን ብቻ፣ ሌላው ዝናብ ስለ ሆነ ቀጣይ ዓመት ታዩትአላችሁ ብሎ ሹፌሩ በመተበት ሆኖ ወደ ፋሲካይት መለሱን። ቀጣይ ግን የትም ብጓዝ ስለ ከተማው ጠይቄ እጎበኝ አለሁ። እንዳልክው እምትማረውን አታቅም። ኩራትም መነሳሳትም ደግሞ ይሰጥ አለ። ታዲያ ግልትምምን መስህብ በመጎብኘት ከተገኘ አብዝቼ ለምን አልጨምርም?”
“አይዞህ ትዞር አለህ ገና። ሀገርህን በ ቀላል ከፈለግህ ግን ዛሬም ዙር። በቀላል እድል ዛሬ ብትነሳሳ አንድ ሺህ ብር ለ ዷክረምቱ ዓመት ሙሉ ብታበጅ አንድ ታሪክአዊ ስፍራ መድረስ ትችል አለህ። ለ ምሳሌ ጢያ ትክል ድንጋይዎች ከእኛ አይርቁም። የቃልኪዳን ምድርአችን፣ ለአሰሳት በእርግጥ ታይቶ አይጠገብም እሚባል ደግ መጠን ያለው መስህብዎች አሏት። ምርጡ ነገር በጉብኝቱ ዓይኖችህ ይገለጣሉ። ሰማኒያ ብሔረሰብ ይሉና ያደነቁሩን አለ። ጥቂቱን ከስሩ ሄደህ እይ። ደስታ ትለምድ አለህ። ብዙ ታውጠነጥንም ደግሞ አለህ፤ ይኖርህ አለ። አንዱ ማህበረሰብ በአንድ ወግ አቅጣጫ ህይወትን ያያል። ሌላው በሌላ። የተለየ ያኗኗሩን መነጸሩ ትንግርት እና ዉበት ነው። ምርጦቹን ደግሞ ለእራስህ ሰብስብ። ችግሮችህን ፍታ። በተለያዩ እይታዎች ማወቅ የችግርህ ብዙ እይታዎችን ማሰስ ትለምድ አለህ። ከተራ ጉብኝት የዘለለ ዋጋ በእርግጥ እንደ አልክው አለ።” ናሆም በመጓዝ እና መጎብኘት የመማር ጉዳዩ ጉዳዩ ሲነሳ በነሆለለ እና የተሳበ ልቡ ላይ መንበልበል እንዲሆን መስ አበረታትቶ ከጨዋታው አያይዞ መከረው። ናሆም በእርግጥ ይህን ቀደም ብሎ ይመኘው ስለ ነበር በመመኘት ለማግኘት እንዲጥር ሲጋበዝ ተስማማ። “ቸር ተመኝ ቸር እንድታገኝ ስለ ሆነ ልክነህ፤ መርኅ አድርጌ የጉዞ-ጉብኝት መሰረት ለመጣል ከእንግዲህ አብዝቼ እመኝ አለሁ። እና ደግሞ ምግብ በእየ ሀገሩ ስለ አለ በመዞሩ ያንን አጠና አለሁ።” የናሆም ህልም ሲበረታ መስ ተጨባጭ ምክር አከለለት። “በእየገጠሩ የተከበሩ ሰዎች ቤት ግባ እና ተጓዥ ነኝ ልረፍ በል። ጥቂት የከተሜ ስጦታ ያዝ። ይቀበሉህ አለ። በደስታ። ስታወጋ እደር ብዙ ትማር አለህ። ግን ስለምግብ ከአነሳህ፣ ቆሎ እንኳ በተለየ መንገድ በእየብሄረሰቡ ይገኝ አለ። በተለያዩ መንገድዎች አዘገጃጅተው ሲጠቀሙ መቀመም ምስጢር ሲሰጥህ የስናክ ገበያ ልታቋቁም ትችል አለህ። ስለ እዚህ በጉዞህ መብል ነአሰራርዎችንም ጠልቀህ በእርግጥ አጥና። እንዴት እንደ እሚሰሩ ለምን እንደ እሚሰሩ ስነሂደቱን ወዘተ. ስታውቅ፣ ያ ከጥበበምርምርህ ከተዋሃደ ደግ አድርገህ ሰንሰለትመብት (ፍራንቻይዝ) መጀመር ትችል አለህ። እና ግንኙነቱስ! በአመትበዓል ብትደውል እያስታወስክ ቤተሰብ በእየ ስፍራው አፈራህ።” ናሆም በመገንዘብ እራሱን ነቀነቀ። አንድ ያዴል ጋሻው ባሩዳ እሚባል ወጣት ተማሪ “አንድ ሂወት ተሠጥቶናል፤ ብዙ ግን ሂወት መዳሰስ አለብን” ያለው ትዝ አለው። ኑሮ አንድ ግዴታ ክፍሉ መንቀሳቀስ ነው። ብዙ ህይወት መመልከት ስለ ሆነ። መስ የአንኮበር ቤተመንግስቱን ሲመለከት ወጣ ብሎ ወደ እፍኝ ከተማዋ ገብቶ ነበር። ሰውዎቹን ሲጠይቅ የእሚታይአቸው የአፈወርቅ ተክሌ መንደር እንኳ ምን እንደ ሆነ አያውቁትም ነበር። ከቀዬ እሚሉት መዉጣት በእድሜዘመን እማይፈልጉት ነገር ነበር። መጓዝ ግን ለሂወት ሰፊ አረዳድ አስገዳጅ ነበር። የናሆምን የተጓዥነት ምኞት መልካም ዕድል ሲመኝለት፣ ናሆም ወደ ነጭዎቹ የሂሳብ መክፈል አዝማሚአ እየተመለከተ በ መዘጋጀት “ተጓዥነቴ ግን እንደ ጉዞ ጦማሪዋ ሳራ ገነነ አይነት አይደለም። ታሪክ ማጋራት እሚችል መክሊት የለኝም። ግን ለግል ጥቅሜ እዞር አለሁ።” የልብልብአቸውን በመጨዋወት እነ ናሆም ቆይተው፣ እንግዳዎቹ መብል ሲአጠናቅቁ፣ በናሆም ፍልስፍና መሰረት ሩብ ሙዝ ለአንድ ተመጋቢ በነፃ እንደ ድህረመብል (ደዘርት) ይሰጥ ስለ ነበር አንድ ከግማሽ ሙዝ በሳህን ለሁሉም እንዲሆን ሰጠ። በማድነቅ ተመግበው ስለ ሃገሩ አየር ንብረት፣ ባህል፣ መስተንግዶ አቅምዎች፣ እና የከተማ አገልግሎት ሥፍራዎችአቸው አተኩረው ሲጨዋወቱ ቀጠሉ፨
ሦስቱ እንግዳዎችም መብል እየአጠናቀቁ በመጨዋወት ላይ ነበሩ። የነጭዎቹ ሃገርን እንደ አወቀ አንዱ በመመልከት ወደ ነጭዎቹ መጠቆም ጀምሮ “በናትህ ተመልከትአቸው በነፃነት ሲጫወቱ! አሜሪካ በድፍረት መናገር እንጂ ፍራቻ የለ። እይአቸው ብሞት!” ከሦስቱ እረዘም ያለው እና ሰፊ ጉርሻ በማንሳት እሚበልጥአቸው ተመጋበከ ገለፀ። ነጭዎቹ በግልጥ ስለ እነ እርሱ እንደ እሚወራ አወቁ። ሌላው ወጣት በጎረሰው ማኘክ ተጠምዶ በመሀል “ምነው አንድ ዋ ይዛኝ ብትሔድ!” በነጥብ አከለ። መብሉን ልክ አጠናቅቀው ከመታጠብ ቀድሞ ሂሳብ ለማውጣት ሲታገሉ ድንገት ሊድ ወደ ሁለትኛው ተናጋሪ ዓይንዎች ልካ ስታየው እና ዓይን ሲገጣጠሙ፣ በልቶ የጨረሰ እጁን በደመነብስ ፀጉሩ ላይ አድርጎ አሻሸ እና እየነሆለለ ለመማረክ ሞከረ። በ ድንቅ መጠን መቅለስለሱ ልክ ሊድ ደንግጣ ዞር ስትል ታወቀው። ከአልታቀደበት ድንገት መቅለስለሱ መልስ ክዉታው ጋብ ሳይል፣ ፀጉሩ ላይ ወጥ እና ፍርፋሪ መጥረጉ ደግሞ ዘግየት ብሎ ታወቀ ው። የበለጠ ሲደነግጥ መንተባተብ ጀመረ። ጓደኞቹ ባያዩም እንደ አላዩ ግን አላየም። “በ..ረ..ሮ ስትነክሰኝ ላባርር አናቴን ወጥ ቀባሁ!” ሁለቱም በበረሮዋ ምትሃት ከት ብለው ሳቁ። ሊድ ጓደኞቿ ከተመለከቱ አስተዋለች። ፊትአቸው ወደ እድለቢሱ ወጣት ስለ አልነበር ምንም አልተመለከቱም። በማፍጠጥ ስለ እማይበረቱ ትኩረት እዛው ነበረች፨

ታጥበው ሲመለሱ የቀረበ ድህረመብል እየተመገቡ ቁጭ በማለት መልስ ጠበቁ። ፀጉር ለቅለቅ ያደረገው ወጣት በመናደድ “በሰው ሃገር ይንቀባረር አሉ!” በማለት አስተያየት ሰጠ። አጠገብአቸው ሃበሻ እሚመስለው አስተርጓሚ ምንም ሳይመስለው ይህን ብሎ ተከታትለው ወጡ። ወዲአው አንዱ እንግዳ መልሶ ሃምሳ ሳንቲም ረስቶ መጣ። ለናሆም ከአዲስ ወጪውን ሁሉ አሰላ። ናሆም በትሁት ልብ ሃምሳ ሳንቲም አጎንብሶ መለሰ። መንጨቅ አድርጎ “አጭበርባሪ!” ብሎ በመሳደብ ወደ ዉጭ በፍጥነት ተወረወረ። ወደ በሩ ሲጠጋ ሲደርስ ነጭዎቹን አፍጥጦ ተመለከተ። አስጊ አኳኋን መስሎ ታየአቸው። ግን አደጋው ትነሽ ነበር። “ምን ነበር ዛፍ ሆኜ እነ እርሱ ጋር ቢወስዱኝ!” ብቻ ብሎ እየተመለከተአቸው ተናግሮ በምር ቅሬታ እንደ ሆነ ወጣ። እንደ ወጣ በትልቁ በማሳል ጉሮሮ ሲጠርግ ስለ ተናገረው ጠይቀው መጨዋወት ጀመሩ፨

“ቆይ ይዛኝ ብቴድ ሲል፤ ሰው ሃገር ሊኖር ተመኘ። ላልነኩት ነገር ግን ነፃነትአቸውን ለምን ተቸ?” ናሆም መሰደቡን ትቶ መስን አወጋ። ‘መሰደቡ የሥራ አይነት ነው! መመረቅ መልሱ ነው!’
“አምላክ ሊሆኑ ቢችሉስ? ለእንግዳ ያላስተናገደ እኔን አላስተናገደ ነው ፍርድቀን ቃሉ! እንግዳተቀባይነትአችን ቀረርቶ ፉከራው ሆኖ ተግባሩ እጅእጅ እሚል መስተንግዶ አለበት።” መስ አከለ እና ለምን አሜሪካ እንደ እምትማርከን አሰበ። “ሰብእአዊነት መናፈቅ ነው! ክብር እና ፍቅር፣ ሰው እንደ መሆንህ ብቻ ሊከፈልህ ስለ እምትፈልግ!” ከ ምናቡ ተጫውቶ ናሆምን ጠየቀ። “አሜሪካ ሰው በመሆንህ እንደ እምትከበር ምንም ቢሆን ማንም እንደ እማይነካህ ይታሰብ አለ። ያ የሰው ሁሉ የህልም ዓለም ነው! የመነካቱ ጉዳይ ስለ አሳመመን እና ስለ ዛልን፤ በ ሰውነትአችን ስለ አልተከበርን እንጂ ድሃነቱ መሆኑ ብቻ አሜሪካን አላስመለከተንም ባይ ነኝ።” ነጭዎቹ ለ መዉጣት ሲወያዩ እየተመለከተ ናሆምም መልሶ ጠየቀ። “እና መፍትሄውስ ግን?” “እንግዲህ አሜሪካን እዚህ አመሳስሎ መጀመር አለብን ባይ ነኝ! ትዉልዱ እስሊቀረፅ ደግሞ እንደ እነ እዚህ ለ ባህል ልዉዉጥ ብዙ ዜጋዎች መጋበዝ እና ዳያስፖራ እንዲበዛ ወደ ሃገርቤት መጥራት! ያሜሪካን ሃልዮታ የ አስጨብጡን አላ!” መስ በ ሰጠው ሃሳብ ናሆም ወደ ምርአዊነት ጨዋታው ስለ ገባ “ዲያስፖራ እኮ ኩራተኛ ብቻ ነው!?” ክፍተቱን ተመልክቶ ጠየቀ።
“የአ አይደል እምልህ! ይኩራ! አንተ አንገት ድፋ ታዲአ! እራስህን እንድትፈትሽ አደል እሚአደርጉህ! ሃልዮታ ከ ገባህ መማር የ አለብህ አንገት ደፍቶ መስራት እንደ አለብህ ነው። መቻቻል፣ መታገስ አለብህ። የአኔ ለእራስህ የፈለግከውን ለመሆን መብት ለእራስህ ሰጠህ ማለት ነው። ማንም እንደ አሻው ከሆነ እኮ፤ አንተም የ እምትመኘውን ልትሆን አልታሰርክም ማለት ነው። የአኔ ለማን ስል ድሃ ሆንኩ ትል ትፀፀት አለህ። ማህበረሰብ ቀድሞ ምንም አይፈልግብህማ! ለሃገር ድሃ እንደ ሆንን ነው በስዉር እምናስበው። ምክንያቱም ሰው ፈርተን ነዋ ሥራ ባለመናቅ እማንሰራው እኮ። ሰው እምንንቀውን ሥራ ሲሰራ ሌላው ከአየ መዋረድን ሁሉም ወገን መረዳቱ አለ። እማንሰራው ድሃነቴ ለሃገሬ ህዝብ ዓይን ከመዋረድ እና ሃብታም መሆኔ ይበልጥ አለ ስለ እምን ነው። እና ዳያስፖራ ቢኮራ ዝቅ ከአላልክ የሰው እንደ አሻ መሆን አልፈቀድክም። ማለትም አንተም እንደ አሻህ መሆን አልፈቀድክም ማለት ነው።”
“ለነገሩ የቴዎድሮስ ለገሰው የፌስቡክ አርበኞች ላይ አንገትአቹህ ይደፋ እምትል አለች ሀበሻ እምትሳደብ!”
“ስወድድኣት!! ድሃዎች እዩ ቅኑ ብላ አጥንት ስትበላ፣ ስትሳደብ እራካ አለሁ! ስድብ ግን ጠልቼ አደለም። ድሃ ዝቡንም ጠልቼ አደለም። ቅኔውን ፈትቼ ነው። መልእክቱ መተሳሰብ የልጅ መቆንጠጥ እንጂ መበሻሸቅ አይደለም። እናት አባት በአሃዝአዊ ስነልቦና ልጅ አያሳድጉም። በቻሉት ጠቅላላ ስነምግባር እንጂ። ዘመኑ ደግሞ ተፋፍሞ ወላጅ እማያቀው ዝመና ዉስጥ ወጣቱን ተደብቆ በመናቅ እና መሳደብ እንዲችል አድርጎ አሳበደው። ይቺ እና ጓደኞቿ የአሃዝአዊ ዓለሙ ወላጅአልባ ሃበሻ ወላጅዎች የሆኑ ናቸው ማለት ነው። እዉነትም የሃገር አርበኛዎች! በጭቃ በመጨማለቅህ እሚቆነጥጥ ወላጅ አለ። በፌስቡክ ብልግናህ እሚቆነጥጥ ወላጅ ገና ሀሁ ስለ አልጨረሰ የለንም። ለመቆንጥጥ እሚወጡ ናቸው እነ እዚህ እንግዲህ። የታሪክ ገፅዎች አድምቆ እሚፈልግአቸው ሰውዎች አይነት ናቸው። ልእለጀብደኛ አርበኛዎች። የፌስቡክ ምትሃትን መገደብ (ቻናል) ማድረግ አቅቶት ዘመኑ ጠፋ። ግድቡን አርበኛዎቹ ለሃገሩ መስራት ጀመሩ። እናትህ እርቧት ፌስቡክ ለመጎርጎር ብር አታጣም። ለስድብ። ስራውስ ጭራሽ? ኧረ አሃዝአዊ ስነምግባር የለም። ኮርኳሚ የለም!” ናሆም በማብራራት ቆይቶ ወደ ቤቱ ጣሪአ ተመለከተ። ነጭ ጨርቁ በደግ አወጣር ዘልጎ በመራቅ ተዝናንቶ ነበር። ቤቱ መዝለጉ ለልጅዎቹ መልካም የነገ ሥነልቦናዊ መዋጮ ነው ብሎ መስ ይህን መምረጡ ናሆም አሁን በተግባር ሲጥመው ተረዳ ው። ትልቅ ቤት ማየት ልብ የአሰፋ አለ። ሲአድጉ፣ ቤቱን ተመልክቶም በትንሽ ደሳሳቤት አደግሁ ብሎ አለመፀየፉን አለማፈሩን እና ከቤት ለመራቅ መፈለጉን ይነጥቅ አለ። በትልቅ ቤት ልብ ትልቅ ሆና ታድግ አለች። ናሆም አያይዞ አሰበ። አሜሪካዎች ትልልቅ እሚአስቡት ትልልቅ በርገር ትልወቅ መኪና ትልልቅ ቤት ትልልቅ ማንነት ስለአላቸው ነው ብሎ ሰሞኑን አንድ የ ኢሳት ጋዜጠኛ ያወራው ትዝ አለው። በሃሳብ መዋጡ ሳይታወቀው ነጎደ። ‘እዉነት ትልቅ ዓለም በዙሪአ ሲገነባ ትልቅ ይታሰብ ከሆነ ምን ያክል ተሸወድን፤’
ወዲአው ሳይታሰብ ስምንት ሰዓት ሆኖ እንግዳዎቹ ናሆምን ከጨዋታው መሀል ጠሩት። በድርድር ጭምር ተነጋግረው በመጨረሻ በደስታ ጎላ ከ አለ ጉርሻ ጋር ሂሳቡን ከፈሉ። አመሻሹ ላይ ለ መመለስ ቀጠሮ ይዘው በትልቅ ምስጋና እሚን አስጠርተው በማስወጣት እና በመመረቅ “እግሲር እስትለን” ብለው በመጨረሻ አማርኛ ሁሉ በማከል ተጨባብጠው ወጡ፨
በመስተንግዶአቸው እሚለያዩ የታዳሚ አይነትዎች እየመጡ መቋቋም ቀጠለ። ደግ መላመድ በደግ አያያዝ ቀጠለ፨

በዕለቱ ማብቂያ የቤተሰቡ አባሎች ጠቅልለው ወደ ዋናው ቤት እንደገቡ፣ እሚ ቤቱን በመዘጋጋት ሳለች አንድ ደንበኛ መጥቶ ይዞት እሚሄደው መብልን አዝዞ አንድ ወሬ ከተቀመጠበት ሆኖ ሹክ አላት። ያላሰበችው ቀጠን ያለው እንግዳ፣ እራሱን የሐረግ ቀድሞ ሠራተኛ አድርጎ አስተዋወቃት። እሚ ስትገረም፣ እና ስታስተናግደው አንድ ወሬ አሳለፈላት። ቀጫጫው ሰው አምሽቶ የመጣው ነገ ወደ አዲስአበባ ስለእሚሄድ እና እነገዛኸኝ ‘የግድ አድረህ ቢሆንም ለወይዘሮ እማዋይሽ መልእክት ስጥልን’ ብለውኝ ስለነበረ ነው አለ። እሚ ክው አለች። ወደ ሱዳን ለመውጣት ጎንደር የእመከሄዱ እንደሆኑ ለመጨረሻ ጊዜ ሲገናኙ ነግረዋት ነበር። “አላቆይቦት እንጂ ዜናው እማ አቶ በረከት ባለቤቶት ከሱዳን እደተገኘ እና እንደሚመለስ መናገሩን እና እነገዛኸኝም እንዳነጋገሩት እና ሠሞኑን እንደሚመጣ እና በባህሪውም መልካም ለውጥ አድርጎ በመናፈቅ ላይ እንዳለ ነው የነገሩኝ።” ቀጭኑ ሰው ይህን ሲናገር እሚ ክውታ ዋጣት። ትልቅ ደስታም ወረራት። ብሩ እና ናሆም በመቆየቷ ሊመለከቷት ሲመጡ ይህን የመጨረሻ ወሬ ሰሙ። ሁለቱም በደስታ ተሞሉ። እሚም አቅፋ መቻቸው። አባታቸው ባህሪውን እንዳሻሻለ፣ እዛ ባይሳካለትም ሲነግድ ከርሞ ስላልሆነለት ለመመለስ እና ከቤተሰቡ ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመቀላቀል ማሰቡን እና ከቶ ገጸባህሪው መስተካከሉን ማወቃቸውን እነገዛኸኝ በመልክተኛው አሳውቀው አንድ ላይ እንዳሉ እና እስኪመጣም አብረው እንደሚሰነብቱ እና እንደሚሸኙት አሳወቋት። መልእክተኛው ጥቂት ተጨዋውቶ እንኳን ደስ አላችሁ በእሚል ቆይታም ደስታቸውን ሲካፈል ቆይቶ በመለየት የረፈደ ስለሆነ መብሉን መውሰዱን ትቶ እዛው ተመግቦ አጨዋውቷቸው ተለያዩ። እነ ብሩ ሸኝተውት ወሬዎችም ጠይቀው ተደስተው ተመለሱ። ‘መች በደረሰ! ቀኖች ባጠሩ’ የቤተሰቡ አውራ እሚሆነው አባት የምር ሊቀላቀል እና ሊደሰቱ ይሆን ዘንድ በመናፈቅ እና መወያየት ተመልሰው ገቡ።

<p class="has-text-align-center" value="<amp-fit-text layout="fixed-height" min-font-size="6" max-font-size="72" height="80">፨፨፨፨፨፨፨፨ ፨፨፨፨፨፨፨፨ ፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨ ፨፨፨፨፨፨፨፨ ፨፨፨፨፨፨፨፨

By Binyamhailemeskel

Hey there! If you want to know about me, I just like fun, commonsense wisdom, and human love. Let us live a bright today changing tomorrow into brighter.
Regards,

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s